በክልሉ የእንስሳት አርቢውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው- የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

ሐዋሳ፤ መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የእንስሳት አርቢውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በየነ በራሳ ተናገሩ ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ  በክልሉ ቦና  እና በንሳ ወረዳዎች  በመገኘት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ሥራን ዛሬ አስጀምረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት በክልሉ በእንስሳት እርባታ ላይ ትኩረት በማድረግ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

የእንስሳት እርባታው  ሂደቱ ኋላቀር በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንስሳት ሀብት ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን አመልክተዋል።

በመሆኑም ከቁጥር በዘለለ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ የእንስሳት ሀብት ልማት ሥራ በማከናወን ዘርፉን ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ  ምንጭ ማድረግ እንደሚስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ አርሶና አርብቶ አደር ከባህላዊ የእርባታ ዘዴ ተላቆ የተሻለ  ተጠቃሚ እንዲሆን ለዝርያ ማሻሻል ስራ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ በዝርያ ማሻሻል ስራ በተያዘው  ዓመት 101 ሺህ እንስሳትን ለማዳቀል ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ተናግረዋል።

እያንዳንዱ አባወራና እማወራ 300 ካሬ ሜትርና ከዚያ በላይ በሚሆን መሬት ላይ የእንስሳት መኖ እንዲያለማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘመቻ መልክ የሚከናወነውን  የዝርያ ማሻሻል ሥራ በአንድ ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመልክተው፤  71 ሺህ ዝርያቸው የተሻሻለ ጥጆች ለማስወለድ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

ይህም በክልሉ ያለውን 11 በመቶ የሚሆን የተሸሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች መጠን ወደ 12 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያሳድገው ጠቅሰዋል።

በቦና ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ  አቶ ታገል ሽብሩ  በሁለት የተሻሻለ ዝርያ ላሞች ጀምረው አሁን ላይ 20 በማድረስ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአንድ የተሻሻለ ዝርያ ያላት ላም በቀን እስከ 25 ሌትር ወተት እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው በመንግስት እየተከናወነ ያለው የዝርያ ማሻሻል ሥራእገዛ እያደረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል ።

በቀን ከ100 እስከ 150 ሌትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት  ካዳቀሏቸው አራት ላሞች አራት ጥጆችን ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ ታገል ዘንድሮ ስድስት ላሞችን በተሻሻለ ዝርያ ላማዳቀል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የበንሳ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኬታ ካቢሶ በበኩላቸው የወተት ላሞችን ዝርያ  በማሻሻል በአሁን ወቅት ሶስት የተሻሻሉ የወተት ላሞች እንዳሏቸው አስረድተዋል።

አሁን ላይ ከአንድ የወተት ላም እስከ 15 ሌትር እንደሚያገኙ ጠቅሰው በወተት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ  ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለከብቶቻቸው የሚሆን የተሻሻለ መኖ በጓራቸው እያለሙ መሆናቸውን አስረድተው፤ ከባለሙያዎች እያገኙ ያሉት ምክርና ድጋፍ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በእንስሳት ልማት ሥራ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም