ቀጥታ፡

በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ በማድረግ "ጣምራ የገበታ ጨው" የማምረት ውጥን ይፋ ሆነ

መስከረም 10/2015/ኢዜአ/ የገበታ ጨውን በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ በማድረግ "ጣምራ የገበታ ጨው" የማምረት ውጥን ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የዓለም አቀፉ የሥነ ምግብ ድርጅት ‘ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል’ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጋራ የገበታ ጨውን በፎሊክ አሲድና አዮዲን የማበልጸግ ውጥን ይፋ አድርገዋል።

በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ የገበታ ጨው የሙከራ ምርትን ለማምረትና ተቀባይነቱን ለመፈተሽ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በጽንስ ወቅት የሚፈጠሩ የነርቭ ሕዋሳትን ቱቦ የአፈጣጠር እንከኖችን የሚቀንስ እና በወሊድ ዕድሜ ክልል የሚገኙ እና ታዳጊ ልጃገረዶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።

በኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የተወጠነው ንድፍ በኢትዮጵያ የሚመረት የፎሊክ አሲድና የአዮዲን ንጥረ ምግቦች የተካተቱበትን "ጣምራ የገበታ ጨው" እንደሚመረት ታውቋል።

በኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የተወጠነው ንድፍ ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ልገሳ  ይተገበራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሣይ ኃይሉ በመግለጫቸው በውጥኑ ላይ እየተካሄደ ያለው ወርክሾፕ የሚካሄደውን ምርምርና አፈጻጸሙን ይበልጥ የሚያዳብር መሆኑን ገልጸዋል።

ምርምሩ ፖሊሲ አውጭዎችና የፕሮግራም ቀረጻ ለሚያካሂዱ አካላት ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ ጨው መጠቀም የፖሊሲ አቅጣጫ ሆኖ ስለተቀመጠ በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ይቀርፋል ብለዋል።

የኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ምክትል ዳይሬክተር ግርማ ማሞ፤ ወርክሾፑ ውጥኑን በስኬት ለመተግበር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ጠቃሚ ግብአቶች ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ከኢትየጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የምግብና ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በምርምሩም የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ-ዴቪስ ዋናውን የምርምር ዘርፍ የቴክኒክ ክትትል ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

‘ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል’ የኢትዮጵያ መንግሥት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የነርቭ ቱቦ እንከኖችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

በሕፃናትና በእናቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው ያልተመጣጠነ ምግብ የኢትዮጵያን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 16 ነጥብ 5 ከመቶ በብር ሲሰላ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እያሳጣ ነው ተብሏል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዳይሬክተር በቀለ መኩሪያ፤ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ምርታማነት ባልተመጣጠነ ምግብ የተነሳ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የምግብ ማበልጸግ ፕሮግራም ቀርጾ ፋብሪካዎች የምግብ ዘይት፣ ጨው እና የስንዴ ዱቄት ለማበልጸግ በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በፎሊክ አሲድና በአዮዲን የበለጸገ ጨው ለማምረት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም