ማህበሩ ከ400 ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከ400 ለሚበልጡ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ዲላ፤ መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዲላ ቅርንጫፍ በጌዴኦ ዞን ከ400 ለሚበልጡ ተማሪዎች ከ200 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጭ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ዳካ ዛሬ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ ለአንድ ተማሪ አንድ ደርዘን ደብተር፣ እስክሪፕቶና እርሳስን ያካተተ ነው።
ለትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጭ መደረጉን ጠቅሰው ድጋፉ ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
የዲላና ጨለለቅቱ ከተማ፣ ወናጎ፣ ይርጋጨፌና ዲላ ዙሪያ ወረዳዎች በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ከ400 በላይ ተማሪዎች የድጋፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በትምህርት ዘመኑ በአቅም ውስንነት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ድጋፉ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል።
ማህበሩ በዞኑ በተለያዩ የበጎ አገልግሎት ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡም ህጻናት በመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከደጋፉ ተጠቃሚ ተማሪዎች ወላጅ መካከል የዲላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፈቲያ ሱልጣን በመማሪያ ቁሳቁሶች ዋጋ መጨመር ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ለሁለት ልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማግኝታቸውን አመልክተው፤ ይሄም ልጆቻቸው ያለምንም ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው የቆፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኢየሩስ መኩሪያ በበኩላ ድጋፉ ትምህርቷን በአግባቡ ለመከታተል እንደሚረዳት ገልፃ፤ለተደረገላት ድጋፉ ምስጋና አቅርባለች።