አሸባሪው ህወሃት ሀገር የማፍረስ ዓላማውን ለማሳካት ልዩነት የዘራ የህዝብና ሀገር ጠላት ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት ሀገር የማፍረስ ዓላማውን ለማሳካት ልዩነት የዘራ የህዝብና ሀገር ጠላት ነው - ምሁራን
አርባ ምንጭ መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከአመሰራረቱ ጀምሮ ሀገር ለማፍረስ የነደፈውን ዓላማ ለማሳካት ህዝቡን በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል የተቃወሙትን ደግሞ ለከፋ ስቃይ ሲዳርግ የነበረ ሽፍታ ቡድን መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ካሱ ጡሚሶ እንዳሉት ህወሃት ከአመጣጡ ጀምሮ በህዝብ ይሁንታ ሳይሆን በነፍጥና በታሪካዊ ጠላቶች ጋላቢነት ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ ተሸክሞ ነው ብለዋል።
በሃይል በትረ ስልጣኑን የጨበጠ በመሆኑም ባለፉት የስልጣን ቆይታውም ራሱን ነጻ አውጪ አድርጎ በማቆየትና በጉልበት አገር ሲዘርፍ መቆየቱን አስረድተዋል ፡፡
ሀገር የማፍረስ ግቡን ለማሳካት ህዝቡን ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እንዲጎላ ሲሰራ የቆየ "ወንበዴ ቡድን" መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በህዝብ ማዕበል ስልጣኑን ሲለቅ የአገሪቱን የጦር መሣሪያ ለመንግስት ማስረከብ ሲገባው መቀሌ ይዞ በመግባት በአገራችን በተለያዩ ክልሎች ህዝብን እርስ በርስ በማጋጨት "ለሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ውድመት የዳረገ የኢትዮጵያ ጠላት ነው" ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከቆመለት ዓላማ አንጻር ሉዓላዊ ከሆኑ አገረ መንግስ ጋር እንጂ በአንድ ሀገር ውስጥ በአሸባሪነት ከተፈረጀ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደማይገባቸው አመልክተዋል ፡፡
ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላባቸው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርስ ዝምታ የመረጡ አለማቀፍ ተቋማትና አንዳንድ ሀገራት ለአሸባሪ ቡድን በመወገን እያደረጉት ያለው አድሏዊ እንቅስቃሴዎች ታሪካዊ ስህተት ነው ብለዋል።
ህወሃት የአገራችንን ህዝብ ህይወት በከንቱ በመቅጠፍና ለዘመናት የተገነቡ የልማት አውታሮችን በማውደም አገርን በታሪክ ይቅር ለማይባል ኪሳራ የዳረገ ቡድን ነው ያሉት ደግሞ የህግ ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ጎድሰንድ ኮኖፋ ናቸው፡፡
"ዓለም አቀፍ የሽብርተኞች ህግ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የሚቀየር አይደለም" ያሉት ምሁሩ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሸባሪ ቡድንን ከህጋዊ መንግስት ጋር አቻ አድርጎ ማየት በራሱ የዓለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ስለዚህ በሰብአዊ መብት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚዳዳቸው "አንዳንድ የህወሃት የውጭ ክንፎች አደብ ሊገዙ ይገባል" ነው ያሉት፡፡