ጉባኤው በሠላም ግንባታና በአብሮነት ዕሴቶች ዙሪያ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል አምስተኛ ቅርንጫፉን በደቡብ አፍሪካ መሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው በሠላም ግንባታና በአብሮነት ዕሴቶች ዙሪያ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል አምስተኛ ቅርንጫፉን በደቡብ አፍሪካ መሠረተ
መስከረም 10 2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሠላም ግንባታና በአብሮነት ዕሴቶች ዙሪያ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል አምስተኛ ቅርንጫፉን በደቡብ አፍሪካ መመሥረቱን ገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሠላም ግንባታ ፣በአብሮነት እና በመከባበር የጋራ ዕሴቶች ዙሪያ የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ ለመስራት፣ ተቋማዊ ጥንካሬ እንዲፈጠር ለማስቻል በተለያዩ ሀገራት ቅርንጫፎች እየመሰረተ መሆኑን የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ውጭ አምስተኛ እና በአፍሪካ ደረጃ ሁለተኛውን ቅርንጫፍ በደቡብ አፍሪካ ፣ፕሪቶሪያ መክፈቱን ገልጸዋል።
ፕሪቶርያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሁሉም ቤተ እምነት ከወከሉ የሃይማኖት አባቶች ጋር በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ዛሬ መስከረም 10 /2015 ዓ.ም የጉባኤው ምስረታ ተካሂዷል ብለዋል።
በመመስረቻ መድረኩ የጉባኤውን ቅርንጫፍ የሚመሩ የቦርድ አባላት ከሁሉም ቤተ እምነት የተወከሉ አባቶች መመረጣቸውን አክለዋል።
በተጨማሪም በመድረኩ ላይ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር በወቅታዊ የሀገር ጉዳይ ላይ አጀንዳ ቀርቦ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል።
በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ድረስ በአጭር ጊዜ ሀብት ለማሰባሰብ አዲሱ የተቋቋመው ቦርድ ሥራ ለመጀመር ቃል በመግባት ተጠናቋል ብለዋል።