የወርቅ ማዕድን ሀብትን በተሻለ መንገድ ማልማት የሚያስችል የማዕድን አዋጅ ተግባራዊ ይደረጋል- ማዕድን ሚኒስቴር

አሶሳ፤ መስከረም 10 / 2015 (ኤዜአ ) የወርቅ ማዕድን ሀብትን በተሻለ መንገድ ማልማት የሚያስችል የማዕድን አዋጅ ተግባራዊ እንደሚደረግ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

በወርቅ ምርት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ውይይት ትናንት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአገር አቀፍ ደረጃ የወርቅ ማዕድን ሀብትን በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የተደረገው ጥረት ውጤት አስገኝቷል ብለዋል፡፡

ከአገራዊ ለውጡ በፊት ወጥቶ የነበረው የማዕድን አዋጅ የወርቅ ኢኮኖሚውን የማይደግፍ እና ለምዝበራ በር የሚከፍት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አዋጁ ያለበትን የህግ እና የአሰራር ግድፈቶች ለማስተካከል በአዲስ መልክ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ አዋጅ በተለይም ለወጣቶች የአገሪቱን የወርቅ ማዕድን ሀብት በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

''አዋጁ ትልልቅ የወርቅ ማምረቻ ኩባንያዎችንም የሚያበረታታ ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይሄም የወርቅ ማዕድን ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የብጽግና ጉዞውን ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅ ተግባራዊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ኦሮሚያ ክልሎች ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲሰሩ የነበሩ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች እና ኩባንያዎች ላይ ፈቃዳቸውን የመሰረዝ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው በክልሉ የሚመረተው የወርቅ መጠን እየጨመረ ቢመጣም ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ዋጋ እስከ 200 ብር ጭማሪ በማድረግ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የወርቅ ሀብቱን ወደ ጥቁር ገበያ ለመሰብሰብ የሚደረገው ጥረት ወደ ብሔራዊ ባንክ ለሚገባው ወርቅ ምርት መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በህገ ወጥ ተግባሩ ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት እየወሰደ ያለውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳደሩ አረጋገጠዋል።

ባንኩ በአካባቢው ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ጥናት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ ናቸው።

ወርቅ በስፋት በሚመረትበት መንጌ ከተማ በቅርቡ ቅርንጫፍ ስራ መጀመሩን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀርንጫፎቹ ከአዘዋዋሪዎች እና አምራቾች ወርቅ ለመረከብ የሚያስችለቸውን አሰራር አስመልክቶ ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ወርቅ አምራቾች ምርታቸውን ይዘው እስከ አሶሳ ከተማ የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞ ከመቀነሱም በላይ በጥቁር ገበያ የሚደረገውን ህገ-ወጥ ግብይት እንደሚያስቀር ጠቁመዋል፡፡

በአሶሳ ዞን ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች መካከል አቶ አረቢ አብዱላሂ ''ያመረትነውን የወቅር ምርት ህጋዊ አሰራሩን በተከተለ መልኩ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ነው'' ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ ባህላዊ አምራቾች ወርቅ የሚያመርቱት ያለ መሠረታዊ እውቀት መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚገኝበት መንገድ እንዲመቻችም ጠይቀዋል።

ባህላዊ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታት 50 ግራም እና ከዚያ በላይ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡ የ35 በመቶ ተጨማሪ ማበረታቻ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም