የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ ወደ ፈጣንና አስተማማኝ እድገት እየተሸጋገረ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ ወደ ፈጣንና አስተማማኝ እድገት እየተሸጋገረ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ
መስከረም 10/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ ተሻግሮ ባለፉት አራት አመታት ወደ ፈጣንና አስተማማኝ እድገት እየተሸጋገረ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ።
በጥናቱ ላይ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የገጠር ልማትና የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ማህበር አማካሪ ዶክተር ጭምዶ አንጫላ፤ የተደረገው ጥናት ቀደም ሲል የነበረውን የግብርና ሁኔታና ከለውጡ ወዲህ የታዩትን የዘርፉ ክንውን ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በግብርና ልማት ዘርፍ በለውጡ አመታት የተከናወኑ ስራዎችን፣ የተገኙ ስኬቶችንና የታዩ ውስንነቶችን ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአደረጃጀት፣ የፖሊሲ፣ የቅንጅት፣የትስስርና መሰል ችግሮች በሒደት እየተቀረፉ መምጣታቸው በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል።
የጥናቱ ውጤት እንዳመላከተው የግብርናው ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ ተሻግሮ ባለፉት አራት አመታት ወደ ፈጣንና አስተማማኝ እድገት እየተሸጋገረ ይገኛል ተብሏል።
ከውጭ የሚገቡ የግብርና መሳሪያዎችና ማሽነሪዎች ላይ ተጥሎ የቆየው ቀረጥ መነሳቱ፤ ለአረንጓዴ ልማት፣ ለአፈር ጥበቃ፣ ለአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ የአረንጓዴ ልማት በተለየ ትኩረት መሰጠቱ ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተለይም የበጋ ስንዴ በመስኖ ማልማት መጀመሩና በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት መቻሉ የሚታይ ለውጥ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
በ2014 በበጋና የበልግ ወቅት ብቻ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ሰብል መመረቱ ለአብነት ተጠቅሷል።
ከበጋ የስንዴ ልማት በተጨማሪ የከተማ ግብርና፣ የቡና፣ የአቮካዶና የአኩሪ አተር ልማት ለግብርናው ዘርፍ የለውጥና እድገት ሽግግር የላቀ ድርሻ እንደነበራቸው አብራርተዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በወጭ ንግድና በግብርናው ዘርፍ የተከናወነው የላቀ አፈፃፀም ኢትዮጵያ በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየተፈተነችም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።
የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ተግባራት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን በ2015 በጀት ዓመትም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።