ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሓት የምን ጊዜም የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት በመሆኑ ባለን አቅም ሁሉ እንታገለዋለን - ነዋሪዎች

መቱ/ጊምቢ/ሻሸመኔ መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) ''አሸባሪው ሕወሓት የምን ጊዜም የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት በመሆኑ ባለን አቅም ሁሉ እንታገለዋለን'' ሲሉ የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ሲያልማቸው የነበሩትን የክፋት ምኞቱን መፈጸሚያ እንዲሆነው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በደሎችን ፈጽሟል።

 ቡድኑ እወግንለታለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብ እንኳን ደንታ የሌለውለ ለቡድን አመራሮች ፍላጎት ብቻ የቆመ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

 በተለይም በስልጣን ዘመኑ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መልከ ብዙ በደሎችን ፈጽሟል፤ የኦሮሞ ተወላጆችን አስሯል፣ ምሁራንን ሰውሯል፣ ወጣቱን ገድሏል። 

ይህ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ ተፈጥሮ ከቸረው ሀብት ንብረቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን በማድረግና በመመዝበር ኖሯል። 

ያሰጋኛል ያለውን የብሔሩ ተወላጅ በ'ኦነግ' ስም እየፈረጀ ሲገድል፣ በስውር እስር ቤቶች አስገብቶ ሲያሰቃይ መኖሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። 

ይህ ሁሉ በደል አልበቃ ያለው አሸባሪው ሕወሓት የኦሮሞን ሕዝብ ስቃይ የሚያበዙ የሽብርተኛ ተላላኪ ቡድኖችን ፈጥሮለት መከራውን እያራዘመ ይገኛል። 

የቡድኑ ተላላኪ የሆነው አሸባሪው ሸኔ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ላለፉት አራት ዓመታት በሽብር ቡድኑ ሕወሓት መሪነትና ፈጻሚነት አረመኔያዊ ወንጀሎችን እየፈጸመ ይገኛል። አሸባሪው ቡድን በቅርቡ ባወጣው ሰነድ ላይ ከዚህ ቡድን መሪዎች ጋር በቀጥታ ግንኙነት እያረገ አብሮ እንደሚሰራ ብቻ ሳይሆን ቡድኑን ለፈለገው ዓላማ ሲጋልበው የቆየ መሆኑን አረጋግጧል። 

ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኦሮሞ ወጣቶችና በምሁራን ላይ ያላደረሰው ግፍ፣ ያልፈጸመው በደል የለም ያሉት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች ፤አሸባሪው ሕወሓት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲፈፅማቸው የቆየው በደሎች ከሰብአዊነት ፈፅሞ ያፈነገጡ ይጠቅሳሉ።

በዞኑ የአሌ ወረዳ ነዋሪ አባ ገዳ ጎበና ሮባ እንዳሉት "አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን በመንግስትነት ሲመራ በቆየባቸው ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ በማንነቱ ሲያሸማቅቅ፣ ሲያስር፣ ሲገድልና ከጎሮቤቶቹ ጋር ሲያባለ ነበር" ብለዋል።

የኃይለስላሴ ዘመነ መንግስትን ጨምሮ በዕድሜያቸው አራት መንግስታትን እንዳዩ የሚናገሩት አባ ገዳ ጎበና "እንደ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝብ ላይ ዘግናኝ ግፎችን የፈፀመ ቡድን የለም" ሲሉ ጠቅሰዋል።

የቡድኑ ግፍ ያልገባበት ቤት የለም የሚሉት አባ ገዳ ጎበና፤ በተለይም በኦሮሞ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎችና ፖለቲከኞች ላይ ሲያደርስ የኖረው በደል ስፍር ቁጥር የሌለው እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በክልሉ ሰዎች በአመለካከታቸው ብቻ እየታሰሩ እየተገደሉና እንዲሰደዱ እያደረገ የክልሉ እናቶች ዓይናቸው እያየ ወጣት ልጆቻቸው ላይ ግፎችን ፈፅሟልም ነው ያሉት።

ለኦሮሞ ሕዝብ በብዙ ይጠቀሙ የነበሩ ምሁራን ደብዛቸውን ማጥፋቱ በቅርብ የሚያስታውሱትና ሁሌም የሚያንገበግባቸው ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቅሉ ጠያቂ ትውልድ እንዳይፈጠር መላውን የኦሮሞ ሕዝብ አንገት የማስደፋት ስራ ሲሰሩ እንደቆዩ ነው አባ ገዳው የሚናገሩት።

አሸባሪው ሕወሓት ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ብሔር ብሔረሰቦቿና ፀረ-ሕዝቦቿ ነው" በማለትም ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

በዞኑ የመቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተካ እንድሪስ "አሸባሪው ሕወሓት ከመሰረቱ ለኦሮሞ ሕዝብ ፀር እንደነበረ በ27 ዓመታት ሲፈፅማቸው በነበረው ግፎች አሳይቶናል" ሲሉ ነው የገለጹት።

የሰው ልጅ ሆኖ በሰው ልጅ ላይ ይፈፀማሉ ተብሎ የማይታሰቡትን ወንጀሎች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲፈፅም የኖረ ቡድን ነው በማለትም በምሬት ያነሳሉ።

"አሸባሪ ቡድኑ ለራሱ ጥቅም ብቻ የተፈጠረ፣ የኖረ አሁንም ይህ ጥቅም ለምን ይቀርብኛል በሚል ሐሳብ እየገደለና እያስገደለ ያለ ስለመሆኑ ምስክር አያሻውም" ብለዋል።

በተለይም ሀገሪቱን ለራሱ ብቻ ሲዘርፋትና ሲሸጣት ለመኖር ከነበረው ሕልም የተነሳ ለአገር አሳቢ ምሁራን እንዳይኖሩ ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሲያሰድድ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደረጄ ወልዴ በበኩላቸው "ቡድኑ በአካባቢው ብዙ መከራ ያስከተለ ተግባር ሲፈጽም ነበር" ብለዋል።

 ምዕራብ ወለጋና አካባቢው የቡና አምራች እንደመሆኑ መጠን የዞኑ ሕዝብ ጥሮ ግሮ ካመረተው ምርት እንዳይጠቀም አድርጎት እንደነበርም ጨምረዋል። 

እሳቸው እንደሚሉት የሽብር ቡድኑ ክንድ በአካባቢው የበረታው ደግሞ መነሻውን ፖለቲካ አድርጎ ወጣቶችን ክፉኛ ሲያሰቃይ በመቆየቱ ነው ይላሉ።

 አሸባረው ህወሓት በዞኑ የነገ ተስፋ የሆኑ ብዙ ወጣት ተማሪዎችን ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበር ጸረ ህዝብና አምበገነን ቡድን እንደነበረም ተናግረዋል። 

ይህ አልበቃ ቢለው ‘’የዞኑ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቡናን ገቢያ በራሱ በመቆጣጠር ለ27 ዓመታት ከአርሶ አደሩ በዝቅተኛ ዋጋ እንደፈለገው በመግዛት የአርሶ አደሩንና የዞኑን ነዋሪዎች በኢኮኖሚ እንዲቆረቁዝ አድርጎታል’’ ይላሉ። 

አቶ ደረጄ አክለውም አሁንም ጁንታው በዞናችን ተላለኪውን ሸኔ በመጠቀም ህዝበችን ላይ ከባድ ቁሳዊና ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡  

በዞኑ የግምቢ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ካሊድ ማትዎስ በበኩሉ ጁንታው ግዜ የማይሸረው ጠባሳ በዞኑና በኦሮሞ ህዝብና ወጣቶች ላይ ሲያደርስ ነው የቆየው ብለዋል፡፡  

በዚህም ብዙ ወጣቶች ታስረዋል፣ ተገድለዋል፤ አሁንም አልበቃ ብሎት አሸባሪዉ በዞናችን ተላለኪውን ሸኔ በመጠቀም በተለያዩ አከባቢዎች በህዝብ ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት ተሳትፎ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን እያፈራረሰ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ 

ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በኦሮሞ ብሔር ላይ ያልፈፀመው አስነዋሪና አሰቃቂ ድርጊት እንደሌለ የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። 

ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያደረሰው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲህም ማህበራዊ በደሎች ሕዝቡን ወደ ኋላ የመለሱ ድርጊቶች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ። 

የከተማው ነዋሪ አቶ ደስታ ቱሳ የኦሮሞን ህዝብ ኦነግ ብሎ በመፈረጅ ሕገ መንግስታዊ መብት የጠየቁ ዜጎችን ለሞት፣ ግማሹን ደግሞ እስር ቤት አስገብቶ፣ ኢ-ስብዓዊ ድርጊቶች ሲፍፀምበት ቆይቷል ብለዋል። 

ሌሎችን ደግሞ እስር ቤት ካስገባ በኃላ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ብዙ ዓመታት እንዲስቃዩ ሲያደረግ ቆይቷል ያሉት አቶ ደስታ፤ በወቅቱ የእስር ቤቶች ቋንቋ ሁሉ አፋን ኦሮሞ ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል። 

በተለይም ፊንፊኔ ዙርያ ላላው አርሶ አደሮች በማስተር ፕላን ስም ያለምንም ካሳ ከይዞታቸው ካፈናቀለ በኋላ፣ ከቄየው ተፍናቅሎ መሄጃ ያጣውን አርሶ አደር መልሶ የራሱ ዘበኛ አድርጎ ሲጫወትበት እንደነበረ አስታውሰዋል። 

አሸባሪው ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ብሔር ከብሔር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት በማጋጨት፣ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገርቱ ብሔር ብሔርስቦች ጋር በፍቅር በመቻቻል እንዳይኖር በዳይ እና ተበዳይ አድርጎ በመሳል ህዝብን ሲካፋፍል ቆይቷል ብለዋል።

 አስተያየት ሰጪዎቹ የዚህን አጥፊ ቡድን ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሸ ግዜ ለማጥፋት ሁሉም የሚችለውን ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል። 

በተለይም መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት በዚህ ወቅት ይህንን የመንግስት እንቅስቃሴ የኦሮሞ ሕዝብ በመሉ አቅሙ ሊደግፈው እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እየተዋጋ ካለው መከላከያ ሰራዊት ጎን ቆመው አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አንስተው፤ ሁሉም ይህንን ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ለሰራዊቱ ደጀን መሆን መቻል አለበት በማለት ያጠቃልላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም