ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው--የቱሪዝም ሚኒስቴር

መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ ለቱሪዝም ልመማት ለማዋል የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ2003 ዓ.ም መጋቢት 24 የግንባታ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የህዳሴ ግድብ በህዝቡ ድጋፍና ትብብር ግንባታው ቀጥሎ የሶስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እና የሁለት ተርባይኖች የሃይል ማመንጨት ስራ በስኬት ተከናውኗል።        

የግድቡ መገንባት ዋነኛ ዓላማ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ቢሆንም የሚይዘው ውሃና በአካባቢው ላይ የሚፈጥረው ማራኪ ገጽታ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚሆን እርግጥ ነው።

የጉባን ተራራ ተንተርሶ በሰፊው በሚንጣለለው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ከ70 በላይ ደሴቶችን ፈጥሮ የጎብኚዎች መዝናኛና መናፈሻ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር ሙሳ ከድር በግድቡ ሰው ሰራሽ ሃይቅ የዓሳ ሃብት በማምረት መጠቀምና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል።             

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት በ2009 ዓ.ም በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ኦዲት የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸው ግድቡ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት መሆኑ እንደተለየ አስታውቀዋል።     

ግድቡ በምን መልኩ ለቱሪዝም ሀብትነት መዋል ይችላል? ምን ቅደመ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ የሚሉ መሰል ጉዳዮች ላይ ዝርዝርና ጥልቅ ጥናት ለማደረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን ዘንድሮ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከበር መሆኑንና ግድቡን በተመለከተ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።  

በግድቡ በሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ የጀልባ አገልግሎት፣ ዓሳ ማስገርና ሎጆችን በመገንባት ወደ ስራ የማስገባት እቅድ መኖሩን አመላክተዋል።

35ኛው የዓለም የቱሪዝም ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ "አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም" በሚል መሪ ሀሳብ በቀጣዩ ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከበር መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም