ሕንድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላትን ገለልተኛና ሉዓላዊነትን ያከበረ አቋም መንግሥት አደነቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሕንድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላትን ገለልተኛና ሉዓላዊነትን ያከበረ አቋም መንግሥት አደነቀ
መስከረም 10 /2015 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው ሕንድ በምክር ቤቱ ኢትዮጵያን አስመልክቶ እያሳየች ላለችው ገለልተኛና ሉዓላዊነትን ያከበረ አቋም የኢትዮጵያ መንግሥት አደነቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የህንዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሽአንካር ጋር ውይይት አድርገዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት ለህንድ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ በሀገሪቱ ካለው የኢኮኖሚ እድሎች እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉ ሪፎርም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አሸባሪው ሕወሃት ኢትዮጵያ ላይ ከከፈተው ጥቃት በሻገር መንግስት ለሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ እየሄደበት በሚገኘው እርምጃ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ህንድ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ኢትዮጵያ ከባድ ግዜያትን ባሳለፈችበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ገልተኛ እና ሉአላዊነቷን ያከበረ አቋም ስታሳይ በመቆየቷ የኢትዮጵያ መንግስት ለህንድ ተልቅ ክብር አለው ብለዋል።
የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሱብራህማንያም ጃይሽአንካር በበኩላቸው በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ በሁለቱ ሀገራት መካከል የለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሰፊ እድሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ህንድ የደቡብ-ደቡብ ባለ ብዙ ወገንን በወከል ከምግብ እና ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያየዙ ችግሮችን ለመፍታት እና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ያደረገችውን አስተዋጽኦ ሁለቱም ወገኖች አድንቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በትናትናው እለት በተደረገው የትምህርት ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋግ ዪ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረው 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉበኤ እስከ መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።