ቀጥታ፡

ኢሬቻ ለኦሮሞ ህዝብ የእርቅ ቀን በመሆኑ የተኮራረፈው ይቅርታ የሚባባልበትና የሚታረቅበት ቀን ነው -የአባገዳዎች ህብረት ጉባኤ

አዳማ፣ መስከረም 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢሬቻ ለኦሮሞ ህዝብ የእርቅ ቀን በመሆኑ የተኮራረፈው ይቅርታ የሚባባልበትና የሚታረቅበት ቀን ነው ሲል የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጉባኤ ገለጸ።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 በአዲስ አበባ በማግስቱ መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በቢሾፍቱ የሚከበር መሆኑን የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ባካሄደው መድረክ ወስኗል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢና የጉጂ አባገዳ ጂሎ ማኖ እንደገለፁት፤ ኢሬቻ የምስጋናና የኦሮሞ ህዝብ አንድነት መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

ኢሬቻ ፖለቲካ የለውም ያሉት አባገዳ ጂሎ ማኖ፤ በበዓሉ ላይ ከአባገዳዎች መለያ ምልክት ውጭ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መለያና ምልክቶችን ይዞ መገኘት እንደማይፈቀድም አስገንዝበዋል።

ከክልሉና ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በሰላም አክብረው ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ሰብሳቢው ጨመረው ተናግረዋል።

የህብረቱ ፀሓፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ በበኩላቸው በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አባገዳዎች ከመንግሥት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ለሰላም ዘብ በመቆም በዓሉን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ሊያደርጉ የሚፈልጉ አካላትን ምኞት ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ማምከን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኦሮሞ ቄሮዎችና ቀሬዎች የበዓሉን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅና በማስጠበቅ የህዝቡን ማንነት ለዓለም ማሳየት አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢሬቻ የዕርቅ፣ የይቅርታና የሰላም ዕለት በመሆኑ ይህንኑ የህዝብ እሴት ለዓለም ማህበረሰብ የምናሳይበት ነው ያሉት አባገዳው፤ ኢሬቻ ምንም አይነት የፖለቲካ ፍላጎት የሚንፀባረቅበት አይደለም ነው ያሉት።

አባገዳ አሊይ ሙሀመድ ሱሩር በበኩላቸው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በገዳ ስርዓት እንዲመራ ያስቻለ ዘመን ተሻጋሪ የምስጋና ቀን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም