ቀጥታ፡

በመድኃኒት አጠቃቀምና አወሳሰድ ጉድለት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል-የጤና ሚኒስቴር

አዳማ መስከረም 10/2015(ኢዜአ) በመድኃኒት አጠቃቀምና አወሳሰድ ጉድለት በህሙማን ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

4ኛው አለም አቀፍ የህሙማን ቀን “ደህንነቱ የተጠበቀ የመድኃኒት አጠቃቀም ለተሻለ የህክምና አገልግሎት ውጤት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዳማ እየተከበረ ይገኛል።

May be an image of 7 people, people sitting, people standing and indoor

በመድረኩ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በጤና ሚኒስቴር የጤና ክብካቤ ጥራት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ በቀለ ባደረጉት ንግግር በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት በሚከሰቱ ስህተቶች በህሙማንና ጤና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል ብለዋል።

በተጨማሪም ህሙማንን አላስፈላጊ ለሆነ ወጪና ለጤና ዕክል ይዳረጋሉ ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ይህም ለህመምና ለሞት ምጣኔ መጨመር ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ በታዳጊ ሀገራት ባካሄደው ጥናት 134 ሚሊዮን የሚሆኑ ህሙማን ከመድህኒት አጠቃቀምና አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ለጉዳት መጋለጣቸውን ጥናቱ ማመላከቱን ጠቁመዋል።

በህክምና ተቋማት ውስጥ መወገድ በሚችሉና አግባብ ባልሆኑ የመድኃኒት አጠቃቀምና አወሳሰድ ጉድለት ምክንያት ከ4 ታካሚዎች አንዱ ለከፍተኛ ጉዳት አልያም ለህልፈት ሕይወት ሊዳረግ እንደሚችል ገልጸዋል።

በዚህም በህሙማን ላይ የሚደርሰው የስነልቦናና አካላዊ ጉዳት ክፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ብሔራዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ጥራትና ደህንነት ስትራቴጂ ተቀርጾ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃትና ስነ-ምግባር ማዳበር ላይ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኪዱ ሃይሉ ናቸው።

ህሙማን ጥራቱን የጠበቀ መድኃኒት እንዲጠቀሙ በህክምና ወቅት ጥንቃቄ የተሞላበት አገልግሎት መስጠትና በአወሳሰድ ወቅት የህክምና ባለሙያዎች ምክር መከተል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም