አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ከ2ሺህ 200 በላይ ሴቶችና ህጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልሎች ከ2ሺህ 200 በላይ ሴቶችና ህጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል
መስከረም 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሕወሓት አሸባሪ ቡድን አባላት በአፋር እና አማራ ክልሎች ውስጥ ከ2ሺህ 200 በላይ ሴቶች እና ህጻናት ላይ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በቡድን በመደራጀት አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሚኒስትሮች ግብረ ሀይል የምርመራና ክስ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት የጋራ ምርመራ ዉጤቶችን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግስት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል የምርመራና ክስ ኮሚቴ በአፋርና አማራ ክልሎች በሚገኙ ዘጠኝ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥፋቶችን የምርመራ ውጤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሪፖርቱን ረቂቅ አውጥቷል።
የአሸባሪ ቡድኑ አባላት በሴቶችና ህጻናት የቡድን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱ የተመላከተ ሲሆን አካል ጉዳተኞች፣በእስር ላይ የሚገኙ እና ከመኖሪያ መንደራቸው የተፈናቀሉ ሴቶች ለአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ሰለባ ናቸው ብሏል።
ቡድኑ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ 706፣ደቡብ ወሎ 644፣በደሴ ከተማ 290፣በሰሜን ሸዋ 186፣ በዋግኅምራ 142፣ ኮምቦልቻ 49፣ሰሜን ጎንደር 44 ፣ በደቡብ ጎንደር 94፣ በከሚሴ 37 እንዲሁም በአፋር ክልል 20 ሴቶች እና ህጻናት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የአስገድዶ መድፈር እንደደረሰባቸው ተመልክቷል።
የአስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃት የተደረገባቸው ሴቶች ኤች አይ ቪን ጨምሮ ለበርካታ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች መዳረጋቸውን እና በደረሰባቸው የሥና ልቦና ጉዳት ሳቢያ ራሳቸውን ለማጥፋት የተገደዱ እንዳሉም ገልጿል።
አሸባሪ ቡድኑ ሴቶች እና ህጻናትን ብቻ ሳይሆን ወጣት ወንዶችን ጭምር አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በቡድን በመደራጀት የመድፈር ጥቃት ያደረሰ ሲሆን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦቹ የወጡበትን ብሔር ሆን ተብሎ ለማዋረድ ተጠቅሞበታል ይላል ሪፖርቱ።
በመሆኑም በቡድኑ አባላት የተፈጸሙት ወንጀሎች በአለም አቀፍ የሰበአዊ መብቶች፣በአለም አቀፍ የሰበአዊነት ሕጎች እንዲሁም ከሀገሪቱ ሕጎች አንጻር እጅግ አሰቃቂ የሆኑ የመብት ጥሰቶች እና የጾታዊ ጥቃቶች ናቸው ብሏል ሪፖርቱ።