ቀጥታ፡

ለስራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ የቀጣናው አገራት ዜጎችን ወጥ በሆነ የክፍያ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ ነው

መስከረም 09 /2015(ኢዜአ) ለስራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎችን ወጥ በሆነ የክፍያ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ ከቀጣናው አገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሊቀ መንበርነት የምትመራው የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው ፎረም ቀደም ብሎ ጽህፈት ቤት በማቋቋምና አግባብነት ያላቸው ሙያተኞችን በመመደብ የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በፎረሙ ኢ-መደበኛ የሰዎች ዝውውርን በማስቆም ዜጎች ህጋዊ ስርዓትን ተከተለው ወደ ፈለጉት አገር የመንቀሳቀስ መብታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ምክክር እንደሚደረግም ነው ያብራሩት።

ፎረሙ ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዊንን ፍላጎት በስርዓት ለመምራት ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ለስራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች ወጥ በሆነ የክፍያና የስራ መረጃ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ ከቀጣናው አገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ የውጭ አገራት የስራ ስምሪትን ምቹና ህጋዊ ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን ከደቡባዊ የአፍሪካ አገራትና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በፎረሙም ከሁሉም የቀጠናው አገራት የተውጣጡ አካላት በሙያ የታገዘ ቴክኒካል ምክክር በማካሄድ ለቀጠናው ሚኒስትሮች  የፖሊሲ ምክረ-ሃሳብ እንደሚያዘጋጁ አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በዜጎች ክህሎት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ትስስር መስኮች ላይ ሊሰራባቸው የሚገቡ የትኩረት መስኮችን በፎረሙ ላይ ታቀርባለች ብለዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ደዔታው አቶ አሰግደ ጌታቸው ምክክሩ በውጭ አገራት የስራ ስምሪት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለማስቀመጥ ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያም በውጭ አገራት የስራ ስምሪትና ተመላሾች ላይ የሚያጋጥማትን ችግር መለየት የሚያስችል ጥናት ማካሄዷን ተናግረዋል።

ምክክሩም ዜጎቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ በስራ ለማሰማራት የሚችሉ የቀጠናው አገራትን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስርዓትን ለመፍጠር እንደሚረዳ አንስተዋል።

ከውይይቱ ማጠቃለያም በቀጣናው ከሚገኙ 11 አገራት የተውጣጣ ቀጠናዊ የክህሎት ልማትና የወጣቶች ስራ ስምሪት የቴክኒክ ቡድን ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል።

የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም 11 የቀጣናው አገራት የሠራተኛ ፍልሰት ጉዳይን የሚመለከቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቀፈ ነው።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊዎችና የቴክኒክ ሙያተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም