ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ እየታዩ ያሉትን ተስፋ ሰጭ ጅምሮችን ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- ፌዴሬሽኑ

መስከረም 9/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እግር ኳስ እየታዩ ያሉትን ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎቸን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ገለፀ።

ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር በተገናኘ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንድሁም የወንዶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የውል ስምምነት መራዘምን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል።

ፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን፤ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ በብዙ መልኩ ለውጥና እድገት የታየባቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።

የወንዶችና የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ብሔራዊ ቡድኖች በተለያዩ የውድድር መድረኮች ተስፋ የሚሰጡ ጉዞዎችን ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በአፍሪካ መድረክ በቻንና ሌሎችም አህጉራዊ ውድድሮች በክለቦችና በብሄራዊ ቡድኖች የታዩ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ተስፋ የሚጣልባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።

በወንዶች ብሄራዊ የታየውን ጥሩ ጅምር ለማስቀጠልም የአሰልጣኝ ውባቱ አባተ የውል እድሳት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የኢትጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለአፍሪካ ዋንጫ ከስምንት ዓመታት በኋላ ማሳለፉና ብሔራዊ ቡድኑን በቻን ውድድር ላይ ማሳለፉ ለኮንትራቱ መራዘም አይነተኛ ምክንያት ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የአሰልጣኙን ውጤታማ እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ በማስገባት ከመስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆይ የሁለት ዓመት ኮንትራት በ250 ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የውል ስምምነቱ መራዘሙን ገልጸዋል።

በፌዴሬሽኑ ወጪ የሚከናወን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ጨምሮ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችም በውሉ እንደተካተቱ ጠቁመዋል።

በአዲሱ የውል ስምምነትም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሔራዊ ብድኑን በቻን ውድድር ከሌላው ጊዜ የተሻለ ጉዞ እንዲያደርግና በ2023 ዓ.ም ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያሳልፍ ይጠበቃል።

በውድድር መድረክ "ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቀኝ አምኜ ነው ኃላፊነቱን የተረከብኩት" የሚለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከተለያዩ ክለቦች የቅጥር ጥያቄ ቢቀርቡለትም ለብሔራዊ ቡድን ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይነትም ለማሰልጠን መስማማቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን ትልቅ ክብር መሆኑን የሚናገረው አስልጣኙ በቀጣይ የአሰልጣኝነት ሕይወቱ ላይ የሚጨምርለት አቅም ስለመኖሩም አንስቷል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ እግር ጓስ እድገት መቃናት ሁሉም የድርሻውን አስተዋፅኦ እንድያደርግ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም