የወጣቶችን ፍላጎትና አቅም ባገናዘበ መልኩ የቤት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶችን ፍላጎትና አቅም ባገናዘበ መልኩ የቤት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል- የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር
ሀዋሳ ፤ መስከረም 9 /2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የወጣቶችን ፍላጎትና አቅም ያገናዘበ የቤት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትብበር እንደሚሰራ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በወጣቶች ኑሮ፣ የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮች ላይ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው አውደ ጥናት በሃዋሳ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ እንደገለጹት ከሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር አንፃር የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የቤት ባለቤት ለማድረግ የሁሉንም አካላት ትብብር ይጠይቃል።
የወጣቶችን ፍላጎትና አቅም ያገናዘበ የቤት ልማት በግል ሴክተሩና በመንግስት ድጋፍ በመገንባት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ በክልልና ከተማ አስተዳደሮች ዘርፉን ከሚያስተባብሩ ባለድርሻ አካላትና ከምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
አውደ ጥናቱም በወጣቶች ኑሮ፣ የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችና ትስስሮች የመንግስትና የግል ሴክተሮችና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።
ከጥናቱ የተገኘውን ምክረ ሃሳብ ለከተማ ልማት ፖሊሲና የቤት ልማት ስትራቴጂ በግብዓትነት ለማዋል ሚኒስቴሩ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው፤ የሀገር እድገት በቀጥታ ከሰው ኃይል ጋር ስለሚቆራኝ ወጣቱን በኢኮኖሚው ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ለወጣቱ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ዘላቂ የስራ ፈጠራና ተያያዥ ችግሮችን ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምር ሊደግፉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከሼፊልድ እና ዊትስ ከተባሉ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር "ዩዝ ፊውቸር" የተሰኘው የምርምር ፕሮጀክት በወጣቶች ኑሮ፣የስራ ሁኔታና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችና ትስስሮች ላይ ጥናት ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ ናቸው።
ፕሮጀክቱ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች በራሳቸው የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ የሚያስችል እንደሆነም አመላክተዋል።
ምርምሩ ወጣቶችን በባለቤትነት ያሳተፈ ሆኖ በኢትዮጵያ ሀዋሳ እና በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ብሮንክሁትስፕረት የምርምር ናሙናዎች በመውሰድ ጥናቱ እንደተካሄደ አስረድተዋል።
አውደ ጥናቱም የተዘጋጀው የምርምር ግኝቶችንና ምክረ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ለማድረግና ለሃገር ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በማሰብ ነው ብለዋል።
ጥናቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ በደቡብ አፍሪካው ዊትስና በእንግሊዙ ሼፊልድ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ኢንጅነር እሸትአየሁ ክንፉ ናቸው።
ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዘው ወጣት መሆኑን ተከትሎ እያጋጠመ ያለውን የስራ፣ የኑሮና የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል መደረግ ያለበትን ዝግጅት ለማሳየት የተካሄደ ጥናት መሆኑን አውስተዋል።
የጥናት ግኝቱ አሁን ባለው ፖሊሲ ችግሮቹን መፍታት ስለማይቻል ፖሊሲዎችን መከለስ፣ ወጣቱን ታሳቢ ያደረገ አዳዲስ የቤት ልማትና የስራ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ በምክረ ሀሳብ ተመላክቷል ብለዋል።
በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ተገቢውን የስራ እድል እንዲያገኙ፣ እየተፈጠሩ ባሉ አዳዲስ የስራ መስኮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፖሊሲ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ጥናቱ ማመላከቱንም አክለዋል።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት፣የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ምሁራን መሳተፋቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግባለች።