በአፍሪካ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚቻለው ከከባቢያዊ ምሕዳሩ ጋር የተጣጣመ የግብርና በፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚቻለው ከከባቢያዊ ምሕዳሩ ጋር የተጣጣመ የግብርና በፖሊሲ ተግባራዊ ሲደረግ ነው
መስከረም 9/2015 (ኢዜአ) በአፍሪካ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚቻለው ከከባቢያዊ ምሕዳሩ ጋር የተጣጣመ የግብርናን በፖሊሲ ገቢራዊ ማድረግ ሲቻል መሆኑን የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት አስታወቀ።
በኡጋንዳ ተቀማጭነቱን ያደረግው የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት 'አፍሳ' ከ33 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የሶስት ቀናት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጥምረቱ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የአካባቢና ስነ ምህዳር ተቆርቋሪዎች፣ ከአገሬው ሰዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች፣ ኅይማኖት አቀፍ ድርጅቶችና ሸማቾችን በአባልነት ያቀፈ ነው።
የጉባዔው አጀንዳ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የ'አግሮ ኢኮሎጂ' ስርዓትን በመከተል አፍሪካ በምግብ ራሷን እንድትችል የሚያስችሉ ምክር ሃሳቦች ላይ ይመክራል።
አግሮ ኢኮሎጂ ማለት ከብዝሐ ሕይወትና ስነ ምሕዳር ጋር የተጣጣመ ግብርናን ዕውን በማደረግ ለዘላቂ ግብርና እና የምግብ ዋስትና መረጋገጥ አስቻይ ሁኔታዎችን መተግበር ያለመ ነው።
ከወራት በኋላ በወርሃ ሕዳር በግብፅ ሻርማል ሼክ በሚካሄደው 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ማስቻል ላይ ያተኮረ ነው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥብቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ጋረደው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈጠረ ባለው ተጽዕኖ እየተፈተኑ ካሉ አገሮች መካከል መሆኗን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ከለውጥ ቀውሶች በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላይ ጥገኛ ለሆኑ አገራት ስጋት መደቀኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአካባቢና አየር ንብረት ላይ ባላት ጽኑ አቋም የሚደርሰውን ተዕጽኖ ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርጻ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
አየር ንብረት ለውጥ የደቀነውን ስጋትም አገራት አግሮኢኮሎጂን ስርዓት በፖሊሲ ደረጃ እንዲተገበር እያስገደደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚቻለው ከከባቢያዊ ምሕዳሩ ጋር የተጣጣመ የግብርናን በፖሊሲ ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
አፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ 'አግሮ ኢኮሎጂን' የተከተለ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ የግብርና ስርዓት ልትከተል ይገባታል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የአፍሪካን የምግብ ስርዓት አዛብቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ድንበር አልባውን አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመግታት የሁሉንም ትብብር ይጠይቃል ነው ያሉት።
የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት አስተባባሪ ዶክተር ሚሊዮን በላይ፤ በአፍሪካ የምግብ ስርዓትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአካባቢ ስነ ምህዳር ጋር የተጣጣመ የግብርና ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር በሚል ወደ አፍሪካ የሚገቡ አንዳንድ የግብርና ቴክሎጂዎችም የአፈርን ለምነት በማሳጣት ቀጣይ ተጽእኖ የሚያመጡ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።
አፍሪካን በሌላው ዓልም ጥገኛ በሚያደርጉ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያና መሰል ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ከ50 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አፈር የማያበቅላቸው ሰብለች እንደሚኖሩ ገልፀው፤ ከዚህም ባሻገር በኬሚካልና ከውጭ በሚገቡ የዘረመል ዝርያዎች በሰው ጤና እክል እንደሚፈጥሩ በጥናት ተመለክትል ብለዋል።
ለዚህም መፍትሄው ባህላዊና ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን በማጣመር ከአካባቢ ስርዓተ ምህዳር ጋር የተጣጣመ ግብርና ስርዓትን በመተግበር በምግብ ራስን መቻልና ኑሮን መሻሻል ለአፍሪካ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ባሕላዊ አገር በቀል የጥበብ መንገዶችን መከተል፣ ከሥነ-ምህዳር ጋር የተጣጣመ፣ የአፈርና ውሃን የጠበቀ ዘላቂ ግብርና ተያያዥ ስልቶችን በመተግበር የምግብ ሉዓላዊነት ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።
የአግሮ ኢኮሎጂ ስርዓትን ገቢራዊ በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም ይገባልም ሲሉ መክረዋል።