በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ተጨማሪ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደንበኞችን የኤክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ተጨማሪ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደንበኞችን የኤክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዳማ መስከረም 09/2015 በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶች የኤክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ለኢዜአ እንደገለፁት አገልግሎቱ በ2017 ዓ.ም በገጠር ለሚኖሩ ዜጎች ኤሌክትሪክ ለማዳረስ እየሰራ ነው።
በዚህም የተቋሙ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን ዳግም በመከለስ ወደ ተግባር መግባቱን ዳይሬክተሩ ተናግሯል።
በዚሁ መሰረት ከዋናው ግሪዲ 65 በመቶ እና ከግሪዲ ውጭ በፀሐይ ሃይል 35 በመቶ ኤሌክትሪክ ሀይል ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 2 ደንበኞች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና 280 የገጠር መንደሮችና ከተሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል ።
በቀጣይ ሶስት ዓመታትም 3 ነጥብ 6 ደንብኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መቀመጡን አንስተዋል።
ተቋሙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በራሱ ወጪ ለመሸፈን የፋይናንስ ሞዴል መቀየር፣ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትና አቅም ማጎልበት፣ የደንበኞች አገልግሎት ዕርካታ ለማምጣት እየሰራ ነውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው በበኩላቸው በዚህ ዓመት በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ደንብኞችን የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።
የወልድያና የደሴ ዲስትሪክትን ጨምሮ በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት የደረሳባቸውን መስመሮች ጠግኖ ስራ ከማስጀመር ባለፈ 52 ተጨማሪ የገጠር ቀበሌዎች ባለፈው ዓመት አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በጥቅሉ ባለፈው ዓመት 76 ሺህ 300 ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዓመቱ የተሻለ የሃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ፣ የሃይል መቆራረጥና የአገልግሎት መጓደል ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአፋር ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን አሊም እንዲሁ አሸባሪው ህወሃት በመሰረተ ልማቱ ላይ ባደረሰው ጉዳት የሃይል አቅርቦት ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
ጉዳት ከደረሰባቸው 18 ማዕከላት ውሰጥ 12 የሚሆኑትን ጠግኖ አገልግሎት ማስጀመር መቻሉንም ተናግሯል።
በተያዘው ዓመት በክልሉ የተቀሩትን 6 ማዕከላት ወደ ስራ ከማስገባት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል ።