ቀጥታ፡

ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች በሚያደርጉት ቅስቀሳ ህግን እንዲያከብሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ መስከረም 9/2011 ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች በሚያደርጉት ቅስቀሳና በመልዕክታቸው የአገሪቱን ህግ እንዲያከብሩ አራት የፖለቲካ ድርጅቶች ጠየቁ። “የብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ኮሚቴ” በሚል በጋራ እየሰሩ የሚገኙት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት በጋራ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  መግለጫ ሰጥተዋል። ፓርቲዎቹ በሰጡት መግለጫ ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች በሚያደርጉት ቅስቀሳና በተደረጉ የአቀባበል ሰልፎች በርካታ ችግሮች ተስተውለዋል። ችግሮች እንዳይቀጥሉ በሚያደረጉ አቀባበሎችና በሚካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች የሚደረጉ ቅስቀሳዎችና የሚተላለፉ መልዕክቶች የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ብቻ እንዲፈፀሙ ጠይቀዋል። የፓርቲዎቹን መግለጫ ያሰሙት የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ መንግስትም የዜጎችን መብትና ደህንነት እንዲያስከብር ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚደንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደተናገሩት በውጭ አገር ሆነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አክቲቪስቶች በአገር ውስጥ ገብተው የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች "ልዩነትን የሚሰብኩ መሆን የለባቸውም"።አንድነትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች እንዲያተኩሩም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ በበኩላቸው የፖለቲካ ልዩነቶችን እያጠበብን ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ለማውጣት ቅድሚያ ሰጥተን መስራት አለብን ብለዋል። በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በጋራ መስራት አለብን ብለዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ እንደተናገሩት መንግስት ከውጭ ለገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች በተደረጉ አቀባበሎች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከል "አስቀድሞ ባለመዘጋጀቱ ችግሮች ተፈጥረዋል" ብለዋል። በተለይ የመንግስት ባለስልጣናት በሚፈጠሩ ችግሮች በሚሰጧቸው ሐሳቦች የመናበብ ችግርን ማስወገድ አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል። ፓርቲዎቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩና ሌሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩ ጥቃቶች በደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዘዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም