ቀጥታ፡

በአዲሱ የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

መስከረም 8 ቀን 2015 (ኢዜአ)በአዲሱ የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን በመከላከል በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በ2015 የትምህርት ዘመን አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በቅድመ አንደኛ ደረጃ እና በተመረጡ በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚተገበር ይታወቃል።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ መገንባት ትኩረት እንደተሰጠውም ነው የተገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘመኑ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር የትምህርት ቤቶችን አካባቢ ትኩረት ያደረጉ ተግባራት ይከናወናሉ ነው ያሉት፡፡

በዚህም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ተቋማትን ተጽዕኖ የመከላከል ስራ በስፋት ይከናወናል ብለዋል።

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የግብረ-ገብና የዜግነት ትምህርት እንዲሁም ለሥራና ክህሎት ስልጠና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ከአዋኪ ነገሮች በመከላከል በሥነ- ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት አመራሩ ግንዛቤ መውሰዱንም አብራርተዋል።

መልካም ስብዕና ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት የወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣መምህራንና ሌሎችም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ አዋኪ ድርጊቶችን በተደራጀ መልኩ መከላከል የሚያስችል ረቂቅ ህግ በአገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ረቂቅ ሕጉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ሕጉ ወደ ተግባር ሲገባም ችግሩን በመከላከል ረገድ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም