የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ እናስቀጥላለን - ዶክተር ይልቃል ከፍአለ - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ እናስቀጥላለን - ዶክተር ይልቃል ከፍአለ
ባህር ዳር መስከረም 8/2015 /ኢዜአ/ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ እናስቀጥላለን ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ገለፁ።
የኢትዮጵያ የአፈ ጉባኤዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በዚሁ ወቅት ''የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት የምናጠናክርበት ወቅት ላይ እንግኛለን'' ብለዋል።
አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያን በተለያየ መልክ በመከፋፈልና በመነጣጠል ግፍ ሲፈፅም መቆየቱን ገልፀዋል።
ቡድኑ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈፀምና ተከታታይ ጦርነት በመክፈት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየጣረ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም አሁን ላይ ለ3ኛ ጊዜ በአማራና አፋር ክልሎች ጦርነት በመክፈት ንፁሀንን በመግደል፣ ሀብትና ንብረት በማውደም ላይ ይገኛል ብለዋል።
ዶክተር ይልቃል ቡድኑ በመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ በአንድነት እየተመከት እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ይሄን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍ የጋራ እሴቶቻችን በማጎልበት ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን የምንገነባበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ለዚህም እንደዚህ አይነት የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ መድረኮችን በተከታታይ ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ግንባር ላይ አገር ለማፅናት እየተዋደቀ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሁሉም ልጅ ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊ ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ በሚያስፈልግ ነገር ሁሉ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
አሸባሪው ህወሃት ጦርነቱ ከተወሰነ ሃይል ጋር የሚደረግ በማስመሰል የመከፋፈል ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተው ይሄን ሴራ በማክሸፍ የፀና አንድነታችንን ለአለም ህዝብ የምናሳይበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የምክር ቤቶች ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባው የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው።
መድረኩም እርስ በእርስ በመተዋወቅ አንድነታችንና መተባበርን ለማፅናት አስፈላጊ ነው ብለዋል።