ቀጥታ፡

ዳያስፖራው በሀገር ላይ የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመከላከል የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

መስከረም 8 ቀን 2015 (ኢዜአ)መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት የሚፈጠሩ ያልተገቡ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመከላከል ዳያስፖራው የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ጠየቁ።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተዘጋጀው የዳያስፖራ ፐብሊክ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ንቅናቄ ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ የኢፌዴሪ አምባሳደሮች፣ የሚሲዮን መሪዎች፣ የዳያስፖራ አደረጃጀት ኃላፊዎች እና አባላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሣ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዳያስፖራው ሀገሩ በምትፈልገው ሰዓት ሁሉ ከጎኗ በመቆም እያሳየ ስላለው አጋርነት አመስግነዋል።

መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የጀመራቸውን ሥራዎች በማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው፣ መድረኩ ሦስተኛው ዙር ወረራን ተከትሎ የተፈጠሩ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመከት እና የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት እየተከናወኑ ያሉ የፐብሊክ እና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ሥራዎች ያሉበት ሁኔታ ላይ በመወያየት ሥራዎቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ሦስት ሳምንታት ዳያስፖራው ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎችም አበረታች ውጤቶች መመዝገብ መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ ዳያስፖራው ካካበተው የማድረግ አቅም እና የጫናው ግዝፈት እየጨመረ የሚሄድ ከመሆኑ አንጻር ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም