ኢትዮጵያ ባለፈው አመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁማ በርካታ አገራዊ ስኬቶች አስመዝግባለች...አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁማ በርካታ አገራዊ ስኬቶች አስመዝግባለች...አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ
መስከረም 8/2015 /ኢዜአ/ኢትዮጵያ ባለፈው አመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁማ በርካታ አገራዊ ስኬቶች ማስመዝገቧን አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለጹ ::
አምባሳደሩ ይህን ያሉት የ2015 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል በፓሪስ በተከበረበት ወቅት ነው ::
የ2015 አዲስ ዓመት በዓሉ አከባበር ኢትዮጵያውያን፣ ትዉልደ-ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት የሃይማኖት አባቶች በፀሎት አስጀምረውታል::
በእለቱም አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ ባለፈው አመት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ብታሳልፍም በርካታ አገራዊ ስኬቶች ማስመዝገቧን ሲጠቅሱ የህዳሴ ግድብ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌትና የሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመር፣ ብሄራዊ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን እና የስንዴ ምርታማነትን በአብነት አንስተዋል::
ኢትዮጵያውያን እና ትዉልደ-ኢትዮጵያውያን የአገራቸዉን ጥሪ በመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪም አቅርበዋል:: እውነተኛ የአገር ፍቅር ከሁሉም በላይ በተግባር እንደሚገለፅ በማስመር።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጐን በመቆም፣ ለሠራዊቱ ቤተሰብ አባላትና ለተጎዱ ወገኖቻችን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል::
በእለቱም በርካታ አፍሪካውያን የዳያስፖራ አባላትና ፈረንሳውያን ኢትዮጵያ አጋርነታቸውን በማረጋገጥ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል::