ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሃብታቸውና የአንድነት አርማቸው ለሆነው ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን ሊቀጥሉ ይገባል- የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

መስከረም 7/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሃብታቸውና የአንድነት አርማቸው ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመጎብኘት ለአገር ሰላም፤ አንድነትና ለግድቡ ሰራተኞች በቦታው ጸሎትና ምስጋና አድርገዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ የእያዳንዱ ቤተ እምነት የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያን በትብብር እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግድብ የሶሰተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁና ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ሁሉንም ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ እና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰው ልጅ በእውቀትና ችሎታው የአዕምሮውን ምጡቅነት ያሳየበት የጥበብ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጦርነትና በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈች ባለችበት ወቅት አስደናቂ ሥራዎችን መስራት ከቻለች ሰላምና አንድነት ቢጠናከር የበለጠ መስራት እንደሚቻል ህያው ምስክር መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተሰጣትን ሀብት በፍትሃዊነት ለመጠቀም እያከናወነች ያለው የአንድነት መገለጫ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዝዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ፤ ከድህነት ለመውጣት ትልቅ ተስፋ ለተጣለበት የህዳሴ ግድብ ሁሉም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፤ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ማሳያና ከድህነት የመውጫ አንዱ መንገድ የሆነውን የህዳሴ ግደብ ከዳር ለማድረስ የጋራ ትብብርና ጥረታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በዘር፤ በሃይማኖት፣ በቀለም ሳይለዩ አገራቸውን ከድህነት ለማውጣትና ለጎረቤት አገሮች ተጠቃሚነት እየሰሩት ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ  ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ ለአካባቢው አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ለሁሉም ለማድረስ የሃይማኖት አባቶች ግድቡን በስፍራው በመገኘት መጎብኘታችን ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ደማቸውን እያፈሰሱ አጥንታቸውን እየከሰከሱ እንዳሉ ጀግኖች ሁሉ የአገርን ልማት ለማረጋገጥ የአየር ፀባይ ሳይበግራቸው ሌት ተቀን እየደከሙ የሚገኙ ዜጎች ሊደነቁ ይገባል ብለዋል።

ለአገር ሰላምና አንድነት ጉባኤው እያከናወነ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሃብታቸውና የአንድነት አርማቸው ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም