ቀጥታ፡

የዎላይታን ህዝብ ታሪክ ሰንዶ የያዘ መጽሃፍ ለንባብ በቃ

መስከረም 7/2015 9ኢዜአ) "ዎላይታ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ የዎላይታን ህዝብ ታሪክ ሰንዶ የያዘ መጽሃፍ ለንባብ በቃ።

መጽሀፉ በቀድሞ የህዝብ ተወካዮችም ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አማኑኤል አብርሃም ተዘጋጅቶ ነው ለንባብ የበቃው።     

የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የቀደሞ አፈ-ጉባኤ አባዳሉ ገመዳ በተገኙበት በዛሬው እለት ተመርቋል።       

መጽሃፉ የዎላይታን ህዝብ ባህል፣ አኗኗር እንዲሁም በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ የነበረውን ድርሻ በስፋት የዳሰሰ መሆኑ ተገልጿል።     

የመጽሃፉ አዘጋጅ አቶ አማኑኤል አብርሃም፤ ከዚህ በፊት በነበረው ስርዓት አባታቸው ለምለሚቷ ዎላይታ በሚል ርዕስ መጽሃፍ አዘጋጅተው እንደነበር አስታውሰዋል።       

ከሦስት ዓመት ከግማሽ ባላይ የጽሁፍና ዝግጅት ጊዜ የወሰደው መጽሃፉ ወጣቶች በታሪክ ዙሪያ ያላቸውን የእውቀት ክፍተት የሚሞላ እንደሆነም አብራርተዋል።       

የዎላይታ ህዝብ ታሪክ በዚህ መልኩ ማንነቱና ታሪኩ ተሰንዶ መዘጋጀቱ ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክን ለማሻገር የሚኖረው ፋይዳም የላቀ መሆኑ ተናግረዋል።  

ለመጽሃፉ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችም ምስጋና አቅርበዋል።   

የቀደሞው ይህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው መጽሃፍ ጽፎና አዘጋጅቶ ለንባብ ማብቃትና ልጅ ጸንሶ መወለድ ተመሳሳይ ናቸው ብለዋል።   

መጽሃፉን ሳነበው 20 ዓመታትን ወደ ኋላ መልሶኛል ሲሉም ተናግረዋል።   

ለቀጣዩ ትውልድ ማስታወሻ ማቆየት መጪው ትውልድ ትክክለኛ ታሪኩን አውቆ አንድነቱን እንዲያስቀጥል አወንታዊ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል።    

መጽሃፉ ሌሎችም በዚሁ መልኩ የህዝቦችን ታሪክ እንዲሰንዱ የሚያነሳሳ አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።    

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተጋበዙት መካከል አቶ ኤሊያስ አዋቶ፤ ስለመጽሃፉ ይዘት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መጽሃፉ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የዎላይታ ህዝብ ታሪክ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ነበረው? ኢትዮጵያን በመስራት ሂደት ሌሎች ህዝቦችስ ምን ዓይነት ሚና ነበራቸው? የሚለውን በስፋት የዳሰሰ እንደሆነም አብራርተዋል።

የዎላይታ ህዝብ ጥንታዊ ታሪክ፣ አኗኗር፣ ባህል፣ መገልገያ ቁሳቁስ እንዲሁም መገበያያ መንገዶችንም ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።        

በመጽሃፉ ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ በህትመት ሂደቱ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም