መምሪያው ከ48 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጠ

20

ጎንደር መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ ኢንዱትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ48 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

መምሪያው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመቀናጀት በከተማው የኢንቨስትመንት አማራጮችና በብድር አሰጣጥ ዙሪያ ከባለሀብቶች ጋር የምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም እንዳሉት ምንም እንኳ ሀገራችን በወቅታዊ ችግር ውስጥ ብትሆንም የኢንቨስትመንት  ፍሰቱ  እየጨመረ ነው።

መምሪያው በጀት ዓመቱ ለ150 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ ባደረገው ርብርብ ለ257 ባለሀብቶች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።

ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ " ገናንና  ኢድን  በኢትዮጵያ  እናክብር" በሚል ያቀረቡትን ጥሪ  ተቀብለው  የመጡና 7  ቢሊዮን  ብር  ካፒታል ያስመዘገቡ 104 ዳያስፖራዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ባላሃብቶቹ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣  በጨርቃ ጨርቅ፣  በብረታ  ብረት ፣ በኬሚካል፣ በሪል እስቴት እና በሆቴልና ቱሪዝምዘርፎች የሚሰማሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶቹን ግንባታ አጠናቀው በሙሉ አቅማቸው ወደ ተግባር ሲሸጋገሩ ከ22  ሺህ   ለሚበልጠ ወገኖች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል።

መምሪያው ባለሃብቶች የሚያነሳቸውን የተፋጠነ የቦታ አቅርቦት፣ የብድር አገልግሎትና ሌሎች ጥያቄዎች በቅርበት ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"የጎንደር ከተማ ሰፊ የንግድና የቱሪዝም ቀጠና በመሆኗ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም አላት" ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ  ምክትል  ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡

ይህን ምቹ አጋጣሚ ወደ ተግባር ለመቀየርም ባለሀብቱ በራሱ ካሳ ከፍሎ የሚፈልገውን መሬት የሚገኙበት አሰራር መፈጠሩን ጠቁመው፤ የከተማ አስተዳደሩ ለባለሃብቶች 500 ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡    

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሞዝ ባልቤ በበኩላቸው ባለፉት አራት ዓመታት ዲስትሪክቱ  ከ1 ሺህ  ለሚበልጡ ባለሀብቶች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የከተማዋን እድገትና የባለሃብቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግም ለአንድ ባለሀብት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ብድር የሚሰጥበትን አሰራር በመዘርጋቱንም አመላክተዋል፡፡

በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ሙሉዓለም ምልምሌ ከዚህ ቀደም 8 ሚሊዮን  ብር ብድር ለማስፈቀድ ባለሀብቱ አዲስ አበባ ድረስ ለመሄድ ይገደድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በጎንደር ዲስትሪክት በኩል እስከ 30 ሚሊዮን ብር ብድር የሚፈቀድበት አሰራር መዘርጋቱ ባለሀብቱን የማበረታታና ኢንቨስትመንቱንም ለማነቃቃት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

በመድረኩ በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም ላበረከቱ ባለሀብቶችና የንግድ ተቋማት የእቅውቅና ሰርቲፊክት አሰጣጥ ስነ-ስርአት ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም