ቀጥታ፡

የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለሀገር ህልውና፣ ለህዝቦች ሰላምና ደህንነት አኩሪ ተግባር እየፈጸሙ ነው - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል

መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላት ለሀገር ህልውና፣ ለህዝቦች ሰላምና ደህነንት አኩሪ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያን ህልውና፣ የህዝብን ሰላምና ደህነንት በማስጠበቅ ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አመራርና አባላት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።

በመርሐግብሩ ላይ መልእከት ያስተላለፉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ሽልማት በወንጀል መከላከል የላቀ ሚና ለነበራቸው አመራርና አባላት እውቅና ለመስጠት ነው ብለዋል።

ፌደራል ፖሊስ በተደረገው ሪፎርምና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የመፈጸም አቅሙ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላት ለሀገር ህልውና፣ ለህዝቦች ሰላምና ደህነንት አኩሪ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑንና በየትኛውም አጋጣሚ በአገርና ህዝብ ላይ የሚቃጡ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ለመመከት በቂ ዝግጀት መኖሩን አረጋግጠዋል።የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ፤ በበኩላቸው ለሀገር ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅና የተደራጁ ወንጀለኞችን ተቆጣጥሮ ለህግ በማቅረብ ፌዴራል ፖሊስ የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

እውቅና እና ሽልማቱም ለዚሁ ተግባር የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አመራርና አባላትን ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል።

እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው የፖሊስ አባላት እየሰሩ ያሉት ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይህንኑ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህወት ታምሩ ፌደራል ፖሊስ እንዲዘምን በማድርግ ተቋማቸው ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተቋሙ የሰላም ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ለነበራቸው የላቀ ሚና በተመሳሳይ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በእውቅና መርሐ ግብሩ አዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ በተለያዩ በጸጥታ ተቋማት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና የፖሊስ ሰራዊት አዛዥ የነበሩት የ95 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ብርጋደል ጀነራል ያደቴ ጉርሙ ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም