ቀጥታ፡

የተሰጠን እውቅና ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ ነው-- ተሸላሚዎች

መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) ለዘንድሮው መኸረ ልማቱ የዋለውን የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ ሂደት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተሰጣቸው እውቅናና ምስጋና ለተሸለ ስራ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሸላሚዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎትና የግብርና ሚኒስቴር የአፈር የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የምስጋናና እውቅና መርሃግብር ዛሬ አካሂደዋል።

የአፈር ማዳበሪያን ከጁቡቲ ወደብ በማንሳት ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በማጓጓዝ ከፍተኛ አስተዋስኦ በማበርከት ተሸላሚ ከሆኑት መካከል የገዳ ትራንስፖርት  አንዱ ነው።

የገዳ ትራንስፖርት ተወካይ አቶ ጥላሁን ጉታ እንዳሉት በተለይ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ማዳበሪያን የማጓጓዝ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ጠቅሰዋል።

የነበረው ችግር ሳያግዳቸው የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ የግብርና ልማት ተደራሽ የማድረግ ስራ ማከናወናቸውን ነው የገለጹት።

አቶ ጥላሁን  ዛሬ የተሰጣቸው እውቅናና ምስጋና በቀጣይ ለሚሰጡት አገልግሎት አቅምና መነሳሳት የሚጨምር መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ውስጥ የቃሊቲ ደረቅ ወደብን በመወከል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተሸላሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የየብስ ትራንስፖርት መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አበራ ናቸው።

በ2014/2015 የአፈር ማዳበሪያን የማጓጓዝ ተግባርን ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ መከናወኑን የገሉት ስራአስካጁ በማጓጓዝ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር  በቅንጅት ፈጥኖ በመፍታትና መጫኛ ቦታዎችን በማመቻቸት ስኬታማ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተበረከተላቸው እውቅና እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ተቋም ለበለጠ ስራ መነሳሰት የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስ።

ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን ባደረጉት አስተዋጽኦ ሽልምት እንደተበረከተላቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ወልዴ ታደገ ናቸው።

የማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደቱ በተለይ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተሳለጠ እንዲሆን ጥረት ሲያደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው ዛሬ የተሰጣቸው እውቅና እንዳስደሰታቸውና ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የባህር ትራንስፖርት የወጪና ገቢ ሂደቱ እንዲቀላጠፍ ያላቸውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዛሬ በተከናወነው የሽልማት መርሃግብር በተቋሙ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች ፣የደረቅ ወደብ ተወካዮች፣የአርሶ አደር ዩኒየኖች እና ሎሎች አጋር አካላት ተሸላሚ ሆነዋል።

በውጭ ኩባንያዎች ሲከናወን የነበረውን  የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ተግባር ካለፉት ሶስት አመት ወዲህ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት አማካኝነት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም