ለኢትዮጵያ የሰላምና የብልጽግና ጉዞ እውን መሆን ለመተባበር ዝግጁ ነን- አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የሰላምና የብልጽግና ጉዞ እውን መሆን ለመተባበር ዝግጁ ነን- አምባሳደሮች
መስከረም 7/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በሚደረገው ጥረት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ኢራን፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሕንድ ያሉ አገራት ከምዕራባዊያን በተለየ መልኩ የራሳቸው የዘመን መለወጫ አቆጣጠር ስርዓት አላቸው።
በዘመን መለወጫም የተለያዩ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ክዋኔዎች ይቀርባሉ፤ በኢትዮጵያም በተለይም የእንቁጣጣሽ ጭፈራ የበዓሉ ልዩ ድምቀት ነው።
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን አስመልክቶም የራስ ቴአትር እንስቶች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ባደረጉ የተለያዩ ኤምባሲዎች በመዘዋወር "የእንኳን አደረሳችሁ፤ የእንቁጣጣሽ አበባየሁሽ ቤተሰብ ጥየቃ" መርኃ ግብር አካሂደዋል።
የራስ ቴአትር እንስቶችም በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ፣ የደቡብ ኮሪያና የቻይና ኤምባሲዎች በመዘዋወር ለየአገራቱ አምባሳደሮችና የኤምባሲ ሰራተኞቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ የኢትዮጵያ የሰላምና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በሚደረገው ጥረት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተደረገላቸው የዘመን መለወጫ ቤተሰብ ጥየቃ መደሰታቸውን ተናግረው፤ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ ለማገዝም በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግን ሶክሄ፤ 2015 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ለሁሉም የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና የሚለመልምበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተው፤ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና እውን መሆን የደቡብ ኮረያ እገዛ የማይለያት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን፤ የኢትዮ-ቻይናን በትብብር ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት የበለጠ ለማሳደግ መሰል ባህላዊ ክዋኔዎች የማይተካ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ አምባሳደር ሞሃመድ ሳሊም አልረሺዲ፤ የራስ ቴአትር የኪነ-ጥበብ እንስቶች ላቀረቡላቸው ባህላዊ ክዋኔ ምስጋና በማቅረብ፤ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የራስ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ተሻለ፤ እንደ ኪነጥበብ ሙያተኛ አዲስ ዓመትን በድምቀት ለማክበር ከቡሄ በዓል ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በኤምባሲዎች የተደረገው የቤተሰብ ጥየቃም ኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰበብ ግንኙነት ኪነጥበብም የራሱ ድርሻ እንዳለው ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሄዱባቸው ኤምባሲዎችም የየአገራቱ አምባሳደሮች የሰጡት ደስታ የተሞላበት ምላሽ ተነሱበትን ዓላማ ማሳካት የቻለ ዝግጅት መሆኑንም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆኑን በማሳየት ወዳጅ አገራትን እንኳን አደረሳችሁ ብለናል" ያለችው ደግሞ የራስ ትያትር የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪና ተዋናይት ትዕግስት ዋሲሁን ነች።