ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ገጽታ እንዳይገነዘብ እያደረጉ ነው - ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን

መስከረም 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ገጽታ እንዳይገነዘብ እያደረጉ ነው ሲል ዓለም አቀፉ ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ተናገረ፡፡

ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሚቴ በማዋቀር ጭምር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም እንደሚሰራ መግለጹን አስታውሷል፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ህወሃት መንግስት ለሰላም የዘረጋቸውን እጆች ወደ ጎን በመተው ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት መክፈቱን ተናግሯል፡፡

የሽብር ቡድኑ ጥቃት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር ጠቅሶ፤ ዝግጅቱን ካጠናቀቀ በኋላ ጦርነት መጀመሩን አብራርቷል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ለጦርነት በሚዘጋጅበት ወቅት አልሸባብ በሱማሌ ክልል በኩል ጦርነት መክፈቱን ያስታወሰው ጋዜጠኛ አልስቴር፤ ይህም የሽብር ቡድኑ የአልቃይዳ አንዱ ክንፍ መሆኑ ከሚነገርለት አልሽባብ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አመላካች ነው ብሏል፡፡

አልሸባብ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ጥቃት ሲፈጽም ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ግልጽ ግንኙነት ያለው የሸኔ የሽብር ቡድን በጥቃቱ ተሳታፊ መሆኑን አስታውሷል።

በተጨማሪም አሸባሪው ህወሃት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ንጹሃን ላይ ጥቃት ከሚፈጽሙ ታጣቂዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ነው የተናገረው፡፡

በሌላ በኩል የሽብር ቡድኑ የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ እንደተሳተፉ በማስመስል የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ውስጣዊ ችግሮችን የመፍታት በቂ አቅም እንዳለው የሚናገረው ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን፤ ነገር ግን አሸባሪ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ታግዞ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል።

በተለይ አንዳንድ የቡድኑ ፍላጎት ደጋፊ ሚዲያዎች እያሰራጯቸው ያሉ የተዛቡ መረጃዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ገጽታ እንዳይገነዘብ እያደረጉ ነው ብሏል፡፡

አሸባሪ ቡድኑን "በፌደራሉ መንግስት ጭቆና የተደረገበት የነጻነት ታጋይ" በማስመሰል የሚያሰራጩት ዘገባ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑንም ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ተናግሯል፡፡

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ሰላም የማይፈልግና ለቃሉ የማይታመን መሆኑን በትክክል ሊገነዘቡ ይገባልም ነው ያለው።

የሽብር ቡድኑ አሁን ላይ ልጆቻቸውን ለጦርነት የማይሰጡ የትግራይ ክልል እናቶች እርዳታ እንዳያገኙ በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍን በግልጽ ለጦርነት እያዋለ መሆኑንም ነው የተናገረው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በቅርቡ መቀሌ ከሚገኘው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የዘረፈው 570 ሺህ ሊትር የሰብዓዊ ድጋፍ ማጓጓዣ ነዳጅ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች ምንም አይነት ዴንታ የሌለው የጨካኞች ስብስብ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም