ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ በመባል ተሸለመ

መስከረም 7 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እ.አ.አ የ2022 የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ አገልግሎት ሽልማትን አገኘ።

በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የአየር ጭነት አገልግሎት አቅራቢው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሽልማቱን ትናንት በለንደን በተካሄደ ስነ-ስርዓት መቀበሉን “ኤር ካርጎ ኒውስ” አስታውቋል።

ሽልማቱን ያዘጋጀው የኤር ካርጎ ኒውስ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርጎ ዜናዎችን በመዘገብ፣ የኢንዱስትሪውን መሪዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግና ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ ትንታኔዎችን በመስራት ለአለም አቀፍ የአየር ጭነት አገልግሎት ሰጪዎች ሪፖርቶችን በማዘጋጀት የታወቀ ነው።

አየር መንገዱ በተመሳሳይ ዘርፍ ይሄን ሽልማት እ.አ.አ በ2021 አግኝቶ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም