ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በቀጣዩ ሳምንት በአገር አቀፍ ደረጃ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሚከበር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በቀጣዩ ሳምንት በአገር አቀፍ ደረጃ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሚከበር ተገለጸ
መስከረም 7 2015(ኢዜአ ) በአገር አቀፍ ደረጃ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ቀን በቀጣዩ ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሚከበር ተገለጸ፡፡ 35ኛውን የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከትም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በሀገር ውስጥና በውጭ የዓለም ቱሪዝም ድርጅቶች ድረ ገጽ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል በክልሉ ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን 35ኛውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በማስመልከት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
አዲስ የቱሪዝም ስትራቴጂ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም አመልክቷል።
በቱሪዝም ቀን አከባበር በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለአልሚ ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በሀገር ውስጥና በውጭ የዓለም ቱሪዝም ድርጅቶች ድረ ገጽ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ አዲስ የቱሪዝም ስትራቴጂ ይፋ እንደሚደረግና ዓመቱን ሙሉ በሁሉም ክልሎች የቱሪዝም ቀንን ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል።
ይህም በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተለያዩ ችግሮች የተጎዳውን ቱሪዝም ለማነቃቃት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት አምባሳደር ናሲሴ።
በቱሪዝም ቀን አከባበር ላይ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ልማዳዊ አሰራሮች ተቀይረው የተሻለ አሰራር ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
የቤንሻንጉል ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሚስኪያ አብደላ በበኩላቸው የዓለም ቱሪዝም ቀን አከባበር የክልሉን የቱሪዝም ሃብትና የኢንቨስትመነት አማራጭ በማስተዋወቅ ለስራ እድል ፈጠራ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
መርሐግብሩ በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ስራም ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን እ.አ.አ ከ1980 አንስቶ በመከበር ላይ ይገኛል።