ቀጥታ፡

በአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደት ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

መስከረም 7/2015 (ኢዜአ) በ2014/2015 የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የእውቅና አሰጣጥ መርሃግብር ተከናውኗል።

የእውቅና አሰጣጥ መርሃግብሩ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ከግብርና ሚንስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

እውቅናው የሚሰጠው የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደት በስኬት ላጠናቀቁ አካላት ነው።

ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በአስፈላጊው ግዜ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ የሆነ የማጓጓዝ ሂደት እንደነበር በመድረኩ ተገልጿል።

የግብርና ሚንስትር አቶ ዑመር ሁሴን እንዳሉት በተለይ ባለፉት አመታት መላ አለምን ሲፈትን የነበረው የኮሮና ቫይረስ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተከሰተው ጦርነት፣ በአለም አቀፍ ገበያው የማዳበሪያ ዋጋ መናርና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዙን ሂደቱን ፈታኝና ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያውን በማጓጓዝና ለአርሶ አደሩ በማዳረስ ሂደት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በነበረው ቅንጅት ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ መጠን ገዝቶ ለተጠቃሚዎች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊ ከሆኑ ግብአቶች መካከል አንዱ የሆነው የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከ15 በመቶ በላይ መድረሱንም ሚንስትሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው ከሶስት አመታት በፊት የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ስራ በውጭ ኩባንያዎች ይከናወን እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም የነበረው አሰራር የተበጣጠሰ ሂደትና ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ ፈታኝ እንደ ነበር ነው የጠቀሱት።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ አየፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት በኩል እንዲደረግ መወሰኑንም አቶ ሮባ ገልጸዋል።

በዚህም የአፈር ማዳበሪያውን በማጓጓዝ ሂደት 24 ግዙፍ መርከቦች፣26ሺህ ተሽከርካሪዎች፣61 የባቡር ምልልስ የተደረገ ሲሆን 12 በመቶ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሂደት በባቡር ትራንስፖርት የተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም