ቀጥታ፡

የቡና ምርትና ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ማሳደግ ይገባል

መስከረም 6/2015 (ኢዜአ) የቡና ምርትና ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ተሸላሚ ቡና አምራቾችና ላኪዎች ገለጹ።

በ2014 በጀት ዓመት በቡና ወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ላኪዎች እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮችና ቡና ላኪዎች የተሰጣቸው እውቅና ለተሻለ ስራ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

ከሲዳማ ክልል ጭሬ ወረዳ የመጡና በቡና ላኪነት የተሸለሙት አርሶ አደር ለገሰ ሮባ ከዚህ ቀደም በሁለት ውድድሮች በእጩነት እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡

ከቀደሙት የሁለት ጊዜ ውድድሮች ልምድ በመውሰድ አሁን ላይ አሸናፊ ለመሆን በመብቃታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

በቡና ላኪነት እውቅና የተሰጣቸው አቶ ሰይድ ኡመር በበኩላቸው ከውጤታማነታቸው በስተጀርባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልፀዋል፡፡

ይሕው ድጋፍ ተጥናክሮ ቢቀጥልም የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ሌላኛው ተሸላሚ አርሶ አደር አቶ ዮሃንስ ታደሰ፤ ለመጀመርያ ጊዜ 600 ኪሎ ግራም ታጥቦ የተቀሸረ ቡና አቅርበው አንድ ነጥብ አንድ ሚልዮን ብር በማግኘታቸው እውቅናው እንደተሰጣቸው ይገልፃሉ፡፡ከዚህ በፊት በቡና ምርት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የሚናገሩት አቶ ለገሰ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን እየጠቀሙ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ጥራቱን የጠበቀ ቡና ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ዘመናዊ የእጥበት ማሽኖችና መሳሪያዎች መጠቀማቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሰይድ ኡመር ናቸው።

ይሕም ለእውቅናው አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አመልክተው በቀጣይም የተሻለ ስራ እንዲሰሩ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው  ነው የሚናገሩት።የቡና ምርት በጥራትና በመጠን ከፍ ብሎ እንዲመረት የሚደረገው ድጋፍና ክትትል በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባም ነው አርሶ አደሮቹና ቡና ላኪዎቹ የተናገሩት፡፡በ2014 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም