ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለመድሃኒት አምራቾች ያለውን ምቹ እድል በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለመድሃኒት አምራቾች ያለውን ምቹ እድል በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
መስከረም 6/2015/ኢዜአ/ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለመድሃኒት አምራቾች ያለውን ምቹ እድል በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ፡፡
ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን አንስተዋል።
በአገልግሎቱ የግዥ መዘርዝር ውስጥ ከተካተቱ 1 ሺህ 20 መድሃኒቶች ውስጥ በ970 ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 25 በመቶ ለሚሆነው መድኃኒት የተመዘገበ አቅራቢ አለመኖሩ ታውቋል።
በተጨማሪም 23 በመቶ የሚሆነው የመድኃኒት አቅርቦት በአንድ አቅራቢ መያዙን እና 49 በመቶ የሚሆኑት አንድና ከዛ በታች የተመዘገበ አቅራቢ ያላቸው መሆኑን ያሳያል።
የአቅራቢዎች ውስንነት ለመፍታት መድሃኒትና የህክምና ግብአቶችን ማስመጣት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት የሚሰጠውን ማበረታቻ በመጠቀም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ወክለው ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዜጎቿን ጤና ለመጠበቅ በዘርፉ እያከናወነች ያለውን ተግባር ዘርዝረዋል።
በጤናው ዘርፍ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት በቂ የመድሃኒት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ ለሚሰማሩ አምራችና አቅራቢዎች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድሃኒትና ህክምና መገልገያ አስመጭነት የተሰማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው በዘርፉ በአምራችነት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በዛሬው ጉባኤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በውላቸው መሰረት መድሃኒት በማቅረብ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚገኙ የገበያ አማራጮች ላይ መረጃዎችን በማስተዋወቅ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎችን መሳብ ዋነኛ ዓላማው መሆኑ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪ በዘርፉ ያሉ አሰራሮችና የቁጥጥር ስርዓቶች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑም እንዲሁ፡፡