ቀጥታ፡

ብሔራዊ መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን ለመከላከል ያግዛል

መስከረም 6/2015 (ኢዜአ) ብሔራዊ መታወቂያ ቀልጣፋና ህጋዊና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን መከላከል ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳለው ተጠቆመ።

የመታወቂያ ቀንን ምክንያት በማድረግ በብሔራዊ መታወቂያ ልማት ዙሪያ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሒዷል።

በ2018 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ መታወቂያ እንዲያገኙ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም ብሔራዊ መታወቂያ በሙከራ ደረጃ በተለያዩ የፌደራል ተቋማት እየተተገበረ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ለማገኘት ተመዝግበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ እንዳሉት የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ለሀገራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ ያበረክታል።

መታወቂያው ግልጽነትና ተጠያቂነትና አካታችና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ መንግስት ለብሔራዊ መታወቂያ እውን መሆን ከህግ ማዕቀፍ ጀምሮ አስፈላጊ ተግባራትን በመፈፀም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ብሔራዊ መታወቂያ ኢትዮጵያ 2025 ተግባራዊ ለምታደርገው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

የሳይበር ወንጀሎችን መከላከልን ጨምሮ የሳይበርና የዜጎችን ደህንነትን ለማስጠበቅ የጎላ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል የዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚከሰቱ የማጭበርበር ወንጀሎችን በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም ቀልጣፋና ህጋዊ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል መተማመንን እንደሚፈጥር አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ አዘዘው የብሔራዊ መታወቂያ ሲተገበር የንግዱ ማህበረሰብን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ አመላክተዋል።

በተለይ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል የነበሩ ማጭበርበሮችን በመከላከል ከንግዱ ማህበረሰብ ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገት የራሱ አስተዋፆ እንዳለው ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መታወቂያ ቀን በዛሬው እለት ተከብሮ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም