መንግስትንና አሸባሪው ሕወሓትን በእኩል ሚዛን ለማየት መሞከር እጅግ የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው - አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስትንና አሸባሪው ሕወሓትን በእኩል ሚዛን ለማየት መሞከር እጅግ የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው - አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ
መስከረም 6 ቀን 2015(ኢዜአ)በህጋዊ መንገድ የተመረጠን መንግስትና አሸባሪው ሕወሓትን በእኩል ሚዛን ለማየት መሞከር እጅግ የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ሲሉ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለጹ።
አምባሳደር ሄኖክ ሽብርተኛ ቡድንን ከመንግስት ጋር በእኩል አይን ማየት ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማወቅ አለበት ብለዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፈረንሳዩ መጽሔት ጂን አፍሪክ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሲሆን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አሸባሪው ሕወሓትን በእኩል አይን ማየት መንግስትን ብቻ ሳይሆን የመረጠውን ህዝብ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው ብለዋል።
እነዚህ አካላት መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማየት ከመሞከር ይልቅ ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር እየተባበሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
“አሸባሪው ሕወሓት ከትግራይ ክልል አልፎ አጎራባች ክልሎች ላይ ጥቃት ከፍቷል፤ይህ ሲሆን እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ መንግስት የለም፤ የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ሀላፊነት አለበት፤አለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን እውነት መቀበል አለበት” ብለዋል።
በተለይ አንዳንድ የምእራባዊያን ሀገራት በግልጽ የአሸባሪ ቡድኑ ደጋፊ ሆነው ሲቀርቡ ታይተዋል ያሉት አምባሳደር ሄኖክ፤ይሁንና እንደ ጣሊያን፣ስፔን እና ፈረንሳይ የመሳሰሉ ወዳጅ ሀገራት ሚዛናዊ እይታ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አሸባሪው ሕወሃት ቡድን አሁን እየተከተለ ያለው የእብደት መንገድ ለብዙ ንጹሃን ሰዎች ሰቆቃ የሚያመጣ ድርጊት በመሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን እኩይ ተግባሩን ከማውገዝ ጀምሮ ቡድኑ ለሰላም ድርድር ቅደሚያ እንዲሰጥ ጫና ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።