በቤኔሉክስ ሀገሮች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለመልሶ ማቋቋምና ልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኔሉክስ ሀገሮች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለመልሶ ማቋቋምና ልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ
መስከረም 6/ 2015 (ኢዜአ) በቤልጂየም፣ኔዘርላንድስና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለመልሶ ማቋቋምና የልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥሪ አቀረበ።
ኤምባሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሸባሪው ሕወሓት “ኢትዮጵያን እኔ ካልገዛኋት አፈርሳታለሁ” የሚል ዓላማ ይዞ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ሶስተኛ ዙር ጦርነት ጀግኖች በከፍተኛ ተጋድሎ በመመከት የአገሪቷን ሉዓላዊነትን እያስገበሩ እንደሚገኝ ገልጿል።
ደጀኑ ሕዝብም ለአገር መከላከያ ሰራዊቱና ለተጎዱ ወገኖች ያለውን በመስጠት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጣ ይገኛል ብሏል።
ስለሆነም በቤልጂየም፣ኔዘርላንድስና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የመልሶ ማቋቋምና የልማት ስራዎች ሳያስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ኤምባሲው ጥሪ አቅርቧል።
በዚሁ መሰረት በአገራቱ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበራሰብ አባላት መንግስት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በከፈተው Euro- 1000439142832 (ዩሮ)፣Usd-1000439142786 (ዶላር) እና Gbp- 1000443606304 (ፓውንድ) ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አካውንቶች ድጋፉን ማድረግ እንደሚችል አመልክቷል።
የውጭ ጉዳይ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር በመተባበር ለአንድ ወር የሚቆይ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች የሚውል ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
በሁሉም አገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ሚሲዮኖች ውስጥ የተደራጁ የገቢ አሰባሳቢ አስተባባሪዎች ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት እና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ድጋፉ እንዲጠናክሩ ተጠይቋል።
ኤምባሲዎቹ ለገቢ ማሰባሰቢያ ምቹ የሆኑ አሰራሮችን በመተግበር የገቢ ማሰባሰብ ስራው እንዲቀላጠፍ የበከሉላቸውን እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።