ቀጥታ፡

ለመከላከያ ሰራዊታችን የደጀንነት ሚናችንን ለመወጣት እየሰራን ነው- የጎንደር ከተማ ሴቶች

ጎንደር፤ መስከረም 6/2015(ኢዜአ) ፡- ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ሚናቸውን በመወጣት አጋርነታቸውን ለማረጋጋጥ እየሰሩ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ ሴቶች ገለጹ፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊት የከተማው ነዋሪ 17 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን የከተማዋ አስተዳደር አስታውቋል።

በጎንደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት እጹብድንቅ ጥላሁን ፤ "ህይወቱን ሰጥቶ የእኛን ሰላም ለሚያረጋግጥልን የመከላከያ ሰራዊት በስንቅ ዝግጅትና ሌሎች ተግባራት ሁሌም ከጎኑ ነን" ብላለች ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱ ከዚህ ቀደም በሴቶች ላይ የፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ለመድገም  በመሆኑ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ በጽናት መታገል አለብን ብላለች።

በዚህም የሴቶችና ህጻናትን ሰቆቃ ለማስወገድ የአካባቢውን  ሴቶች በማስተባበር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበው ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጻለች።

የሽብር ቡድኑ የበርካታ ሴቶችን ህይወት አጨልሟል ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 9 ነዋሪ  ወይዘሮ ሃድያ መሃመድ ናቸው፡፡

የሽብር ቡድኑ ሴቶችን በመግደል፣  አስገድዶ በመድፈርና ህብትና ንብረታቸውን በመዝረፍ ጭምር በታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ወንጀለኛ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶችን የሚዋርድ ፣የሚያፈናቅልና የሚገድል የሽብር ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ እኛ ሴቶች ከሰራዊችን ጎን በመቆም በስንቅ ዝግጅትና በገንዘብ መዋጮ በመደገፍ አጋርነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ግንባር ለዘመተው ሰራዊት የከተማዋ ነዋሪዎች 17 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የስንቅ ድጋፍ አበርክተዋል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ ለሰራዊቱ 76 ሰንጋዎች፣ 488 በጎች፣ 165 ኩንታል ደረቅ ስንቅ፣ 131 ካርቶን ቴምርና 625 ደርዘን እሽግ ውሃ በማሰባሰብ ወደ ግንባር መላካቸውን አስረድተዋል፡፡

የከተማ አሰተዳደሩ የህዝቡን የደጀንነት ተሳትፎ የሚያስተባብር የሎጀስቲክ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡

የከተማውን ሰላም በአስተማማኝነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የ"ብሎክ " አደረጃጀት ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለሰላም ጠንቅ የሆነው የሸብር ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስኪደመሰስ ድረስ ህዝቡ ለሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ያልተቋረጠ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም