በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተግባራዊ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተግባራዊ ይደረጋል
መስከረም 6/2014/ኢዜአ/ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምሕርት ሚኒስቴር በአዲሱ ስርዓተ-ትምህርት እና በ2015 ትምህርት ዘመን ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ስርዓተ- ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ዛፉ አብርሃ፤ አዲሱ ስርዓተ ትምሕርት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችልና በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ስርዓተ-ትምርቱ በእውቀት የታነጹ ዜጎችን ለመቅረጽ ፣አገርን ለማሳደግና ከድህንት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አኳያ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ነው የገለጹት።
አዲሱ ሰርዓተ-ትምህርት ለ9ኛ እናለ10ኛ ክፍል ተማሪዎች በሙከራ ደረጃ በሁሉም ክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥም ነው ያመለከቱት።
ለ9ኛ እና ለ10ኛ ክፍል በአዲሱ ስርአተ ትምሀርት የተዘጋጀው መጻሐፍት ተጨማሪ ግብዓቶች እንዲካተቱበትና አስተያየት እንዲሰጥበት በሚኒስቴሩ ዌብሳይት ላይ እንደሚጫን አረጋግጠዋል።
ግብአቶቹ ከተካተቱ በኋላም በ2016 ዓም ትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በአዲሱ ስርዓተ-ትምህርት ቅድመ አንደኛ ሁለት ዓመት፣ከ1-6 አንደኛ፣7-8 መካከለኛ፣9-12 ሁለተኛ ደረጃ ተብሎ ተቀምጧል ነው ያሉት።
በዚሁ የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ለማድረግም ከአንድኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የግብረገብ ትምህርት እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከአንድኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ባለው እርከን የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ ትምሕርቶችን በማዋሐድ በአካባቢ ሳይንስ ትምህርት እንደሚካተትም አንስተዋል።
ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ደግሞ ከዚህ በፊት በተናጥል ይሰጡ የነበሩ የፊዚክስ፣ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ ትምህርቶች አንድ ላይ ሆነው አጠቃላይ ሳይንስ ተብለው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የጂኦግራፊና የታሪክ ትምህርት የማህበራዊ ሳይንስ በመሆን በአንድ ላይ የተዘጋጁ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የነበረውና የተሻሻለው ስርዓተ-ትምህርት የአገር በቀል ዕውቀቶችን ከማካታት አንፃር ክፍተቶች የነበሩበት በመሆኑም እንዲሻሻል መደረጉን ጠቅሰዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀምር የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴሩ የትምህርት ፕግራሞችና ጥራት ማሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ናቸው።
ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ችግሮች ቢከሰቱም በመምህራን፣በተማሪዎች፣በወላጆችና በሚኒስቴሩ ጥረት ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመት ደግሞ የተሻለ ትምህርት ለመስጠት የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ ውይይትና ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።