ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመዳሃኒት አቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆን በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

መስከረም 06 /2015 (ኢዜአ) ሁለተኛው አለም አቀፍ የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያ አቅራቢዎች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።

ሁለተኛው አለም አቀፍ የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያ አቅራቢዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።

የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎት በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመድሃኒት ገበያ ፋላጎት ቢኖሩም የአቅራቢዎች ቁጥር ውስን መሆኑ ገልጸዋል።

ለአብነትም በአገልግሎቱ የግዥ መዘርዝር ከተካተቱ 1020 የመድሃኒት አይነቶች መካከል በ970 መድሃኒት አይነቶች በተደረገው ጥናት 257 መድሃኒቶች ምንም አይነት የተመዘገበ አቅራቢዎች የላቸውም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት 231 የመድሃኒት አይነቶች በአንድ አቅራቢ ብቻ ያላቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህም በአቅርቦቱና በፍላጎቱ መካከል አለመጣጣም እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው የጤና ሚኒስትርን ወክለው የተገኙት የአርማወር አንሰን ምርምር ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያ አቅራቢዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት በአምራች ዘርፍ ትኩረት ከሰጣቸው አንዱ የመድሀኒት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የግሉ ሴክተር በዘርፉ እንዲሰማራ ጥሪ አቅረበዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ በዘርፍ የሚገኙ የገበያ አማራጮችን ላይ መረጃዎችን በማስተዋወቅ የመድሃኒት አምራችና አቅራቢዎችን መሳብ ዋነኛ ዓላማው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ በዘርፉ ያሉ አሰራሮችና የቁጥጥር ስርዓቶች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም