የማላዊ መንግሥት ልዑካን በዳያስፖራ ተሳትፎ ስራዎች ላይ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር የልምድ ልውውጥ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የማላዊ መንግሥት ልዑካን በዳያስፖራ ተሳትፎ ስራዎች ላይ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር የልምድ ልውውጥ አደረጉ
መስከረም 06 ቀን 2015(ኢዜአ) የማላዊ መንግስት የልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በመገኘት በዳያስፖራ ተሳትፎ ስራዎች ላይ የልምድ ልውውጥ አደረጉ።
የልምድ ልውውጥ መድረኩን ያመቻቸው በኢትዮጵያ የማላዊ ኤምባሲ ሲሆን በመድረኩ ላይ የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክን የሚወክሉ አባላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት አራት አመታት የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማትጋት የተከተለቻቸው ተቋማዊ አደረጃጀቶችንና ህጋዊ ማዕቀፎችን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ለእንግዶቹ አቀባበል ያደረጉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በዳያስፖራ ተሳትፎ ካካበተችው ልምድ ለመማርና ተሞክሯቸውን ለማጋራት በመምጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አፍሪካውያን የሚያካሂዷቸው ተመሳሳይ የእርስ በእርስ መማማሪያ መድረኮች ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ ይህ በተቋማት መካከል የተጀመረ ግንኙነት የሁለቱ ሀገራት ዳያስፖራዎች በሚኖሩባቸው ሀገራት የጋራ ጥምረት በመፍጠር ሊጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
በርካታ ሀገራት በዳያስፖራውና በሀገር ቤት መካከል በፈጠሩት የመተማመን መንፈስና በዘረጓቸው ምቹ ሁኔታዎች ከዳያስፖራ አማራጭ ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው የለውጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሰራባቸው ጉዳዮች መካከል ዳያስፖራውን ከሀገሩ ጋር የሚያቀራርቡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገኝበት አስታውሰዋል።
አክለውም ባለፉት አራት አመታት በዳያስፖራውና በሀገር ቤት መካከል በተፈጠረው የመተማመን መንፈስና የዳያስፖራ ጉዳይን የሚያስተባብር ራሱን የቻለ ተቋም መመስረትን ጨምሮ በተዘረጉ ምቹ ሁኔታዎች ዳያስፖራው በሀገራዊ ልማትና የገጽታ ግንባታ ስራዎች ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላትም ስለተደረገላቸው አቀባበልና ስለቀረበላቸው ተሞክሮ አመስግነው፣ ኢትዮጵያ የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ ባለፉት ሃያ ዓመታት ካከናወነቻቸው ተግባራት በተለይም ባለፉት አራት አመታት ከተገኙ ውጤቶች ጠቃሚ ተሞክሮ መቅሰም መቻላቸውን ገልጸዋል።
ተሞክሮውን በመቀመር በሀገራቸው ተመሳሳይ ተቋም እንዲመሰረት ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያቀርቡ መግለጻቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል።