ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሓትን የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል

መስከረም 6/ 2015(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከነገ በስቲያ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ዋይት ሐውስ ፊት ለፊት የሚከናወነው ሰልፉ የተለያዩ አላማዎችን ያነገበ መሆኑን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ጣሰው መላከሕይወት ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ዳግም ወረራ እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

“አሜሪካ የሽብር ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት በይፋ በማውገዝና ለአፍራሽ ድርጊቱ ተጠያቂ ማድረግ አለባት፣ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም ይኖርባታል” የሚሉ መፈክሮችን እንደሚያሰሙ አመልክተዋል።

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዳግም ልታጤነው እንደሚገባ የሚያሳስቡ መልዕክቶችም እንደሚተላለፉም ነው አቶ ጣሰው የተናገሩት።

ከሰላማዊ ሰልፉ በተጨማሪ በአሜሪካ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማትና ጥምረቶች የአገሪቷ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሚዛናዊ እይታ እንዲኖራቸው የማወያየትና የማስረዳት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያን የሚደግፉ የትዊተር ዘመቻዎች እየተካሄዱ ናቸው ብለዋል።

በተያያዘም አሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተቋቋሙ የሲቪክ ተቋማትና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ በሚካሄደው የአጋማሽ ዓመት(ሚድ ተርም) ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ስራ ላይ የሚሳተፉ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በድምጽ የመቅጣት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኝ ነው አቶ ጣሰው ያስረዱት።

ለዚህም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሚገኙበት ግዛት ማህበረሰቡን የማንቃትና የመቀስቀስ ስራ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን ሰልፍ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት፣ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳጆች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።

አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት ለማውገዝና የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ እየተሳተፉ ላሉ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ፣ለጸጥታ ኃይሎችና ዜጎች ድጋፍና አጋርነትን የመግለጽ አላማ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ ጳጉሜን 2 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም