ቀጥታ፡

በአውሮፓ ሕብረት የውጭ አገልግሎት ቢሮ ቃል አቀባይ በኩል የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የለውም- በቤልጂየም

የኢትዮጵያ ኤምባሲ መስከረም 6 ቀን 2015 (ኢዜአ) በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ አገልግሎት ቢሮ ቃል አቀባይ ፒተር ስታኖ የተሰጠው የመንግስትን ስም የሚያጠለሽ መግለጫ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል አወገዘ።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አሸባሪው ሕወሓት ሶስተኛ ዙር ጦርነት በመክፈት፣ነዳጅን ጨምሮ የሰብአዊ እርዳታን ለወታደራዊ አላማ መጠቀምን ጨምሮ የተለያዩ ግልጽ ጥሰቶችን ወደ ጎን ትተውታል ብሏል።

ፒተር ስታኖ “የሽብር ቡድኑ የአፍሪካ ሕብረትን ሰላምን አማራጭ ተቀብሏል መንግስትን ይሄን አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይገባል፤ መንግስት በመቀሌ የሚፈጽመው የአየር ድብደባ ለሰላም እንቅፋት ፈጥሯል” በሚል የሰጡት አስተያያት አሳሳችና የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ ሰላምን ለማምጣት የወሰዳቸውን ተጫባጭ እርምጃዎች ከግምት ውስጥ ያልከተተ መሆኑን አመልክቷል።

በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የተጠናጥል ሰብአዊ ተኩስ አቁም ማድረጉን እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት ዐብይ ኮሚቴ ማቋቋሙን ኤምባሲው ለቃል አቀባዩ በሰጠው ምላሽ አስታውቋል።

መንግስት በሰላም አማራጩ በመተማመን ውይይቱን ለመጀመር መንገድ የሚከፍት ነው ብሎ እርምጃዎች መውሰዱን ገልጿል።

ኤምባሲው የአውሮፓ ሕብረት የውጭ አገልግሎት ቢሮ ቃል አቀባይ ፒተር ስታኖ “የአንድ ወገን ስም ማጥፋት ተግባር” እንደሚያወግዝና እንደማይቀበልም አስታውቋል።

መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አሁንም የማያወላውል ቁርጠኝነት እንዳለው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም