የአገርን ሉአላዊነትና የህዝብን ጥቅም በመጻረር የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ

መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የህዝብን ጥቅም በመጻረር የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ።

የተቋቋሙለትን ዓላማ አክብረው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶ የመደራጀት መብታቸው ሙሉ በሙሉ እዲረጋገጥ በተሰራው ስራ ከአራት ሺህ በላይ ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል አብዛኞቹ የአገሪቱን ህግ አክብረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥቂቶቹ ግን ከአገርና የህዝብ ጥቅም በተቃራኒ በመቆም በህዝብ ስም የሚመጣን ገንዘብ የሚያባክኑ፣ ምዝባራ የሚፈጽሙና በድብቅ ለውጭ ባንዳዎች ተላላኪ በመሆን የአገር ሉዓላዊነትን አሳልፈው ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአገሪቱ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰፊ እድል መሰጠቱን ጠቅሰው ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው የአገርና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም መስራት ግደታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ዓላማ በተቃራኒ በመስራት የአገርን ሉአላዊነትና የህዝብን ጥቅም በመጻረር የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ባገኛቸው ድርጅቶች ላይ ባለስልጣኑ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውሰው በቀጣይም መሰል የህግ ጥሰት በሚፈጽሙት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ህግ ተላልፈው በተገኙ ድርጅቶች የማስጠንቀቂያ ድብዳቤ የተጸፈ ሲሆን ሶስት ድርጅቶች ላይ ህጋዊ ፈቃዳቸውን የመንጠቅ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

አሁንም የአገርን ጥቅም አሳልፈው በድብቅ አጀንዳ የራሳቸውንና የባንዳዎችን ድብቅ ዓላማ ለማስፈጸም የሚጥሩ ግለሰቦችም ይሁኑ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን በማስጠበቅ ለመቀጠል በምታደርግው ትግል ሳንካ ለመሆኑ የሚጥሩ የሲቪል ማህበራት ካሉ ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል።

አብዛኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለህዝብ ጥቅም የቆሙ አገር በችግር ወቅት በሆነችበት ጊዜ ድጋፍ የሚያደርጉ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ ያደረጉትን የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።  

በቀጣይም ድጋፍ ለማሳባሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ህግና ስርዓትን አክብረው ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት ለመፍጠር ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስርዓት የመዘርጋት ስራ እየሰራ መሆኑንምጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም