''ለኢትዮጵያ አንድነት ዘላቂ ሰላም ዘብ እንቆማለን'' -- የነቀምቴ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
''ለኢትዮጵያ አንድነት ዘላቂ ሰላም ዘብ እንቆማለን'' -- የነቀምቴ ከተማ ወጣቶች
መስከረም 05/2015 ነቀምቴ (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ አንድነት ዘላቂ ሰላም ዘብ ለመቆም መዘጋጀታቸውን የነቀምቴ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
የነቀምቴ ከተማ ወጣቶች በዛሬው ዕለት በወቅታዊ የአገራዊ ሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ አስትያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች መካከል ወጣት ገመቺስ ተስፋዬ በአሁኑ ጊዜ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ አገርን ለማፍረስ እያደረጉት ያለው የጥፋት ዘመቻ የሚወገዝ ነው ብሏል።
በዚህም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በሚደረገው ትግል ውስጥ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም አስላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ለመከላከያ ሠራዊት በሚደረገው ድጋፍም ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን የሚፈለግበትን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግሯል፡፡
የጁንታው ተላላኪ የሆነው ሸኔ የሕዝቡን ሀብትና ንብረት እየዘረፈና እያቃጠል ለኦሮሞ ሕዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር እያሳየ ነው'' ብሏል ወጣቱ።
ይህም በመሆኑ ወጣቱ ይህንን አሸባሪ ኃይል ከፊቱ በመቆም መታገል ይኖትበታል ብሏል፡፡
ወጣት አዲሱ ጉደታ በበኩሉ ''በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ለዘመናት የቆየችውን አገር ዛሬም በወጣቶቿ ትጠበቃለች'' ይላል።
ወጣት አዲሱ በቀጣይ ከመንግሥት ጎን በመቆም የወጣትነት ግዴታውን ለመወጣትና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን አስረድቷል፡፡
ወጣት ሊዲያ ኢዶሣ በበኩሏ አገሪቷን ለማፍረስ እየተሯሯጡ የሚገኙትን ጁንታውንና ተላላኪው ሸኔን በመመከትና ለኢትዮጵያ አንድነት ዘብ ለመቆም መዘጋጀቷን ትናገራለች።
የከተማው ወጣቶችም የአከባቢያቸውን ሠላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ውስጥ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቃለች።
ከዚህም አልፎ ወጣቷ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል የአገራችንን ዳር ድንበር ለማስከበር ዝግጁ መሆኗን ገልጻ ሌሎችም ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፋለች።
የነቀምቴ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቸሪነት አራጋው፤ ወጣቶች ለኢትዮጵያ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በቁርጠኝነት መታገል አለባቸው ብለዋል።
ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የውስጥና የውጪ ጫና በመመከት ሂደት ግምባር ቀደም መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የጁንታ፣ የሸኔና የጽንፈኛ ሀይሎች አገርንና ሕዝብን የማተራመስ ተልዕኮ ለማክሸፍ የአከባቢያቸውን ሰላም እንዲያስጠብቁም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የአገራቸውን ዳር ድንበር መጠበቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ወጣቶች አሸባሪዎች በየአካባቢው የሚያሰራጩትን ፕሮፖጋንዳ ለማክሸፍ መስራት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።