ኢትዮጵያ በጫናዎች ውስጥ ሆና በዓለም የቡና ገበያ መጻዒ ተስፋዋን ያሳየ ስኬት አስመዝግባለች-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጫናዎች ውስጥ ሆና በዓለም የቡና ገበያ መጻዒ ተስፋዋን ያሳየ ስኬት አስመዝግባለች-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
መስከረም 5 ቀን 2015 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ውስጥ ሆና በዓለም የቡና ገበያ መጻዒ ተስፋዋን ያሳየ ስኬት ማስመዝገቧን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
በ2014 በጀት ዓመት በቡና ወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ላኪዎች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ዛሬ እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በዚሁ ወቅት የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት በአገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ተግባራት 'የኢትዮጵያ ቡና በውድ ዋጋ እንዲሸጥና የውጭ ምንዛሪ ግኝት' እንዲጨምር አድርገዋል።
ይህ የለውጥ ትግበራ የኢትዮጵያን መጻዒ ተስፋ ብሩህ ከማድረጉ ባሻገር፤ የአርብቶ አደርና የአርሶ አደሩን ህይወት እየለወጠ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ በአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ 10 ተግባራትን በመለየት ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም መቃረቡን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት 72 በመቶ የሚጠጋው የውጭ ምንዛሪ ከግብርናው ዘርፍ መገኘቱን በማስታወስ ከዚህ ውስጥ 35 በመቶው በቡና ግብይት መሸፈኑን ጠቅሰዋል።
በ2014 በጀት ዓመት የተገኘው አመርቂ ውጤት ታሪክ የማይረሳው መሆኑን በመጥቀስ ለስኬቱ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን በሙሉ የተሰማቸውን አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ከተቋቋመ ጀምሮ ምርትና ምርታማት በማሳደግና ግብይቱን በማዘመን አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
በሀገሪቱ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ኢትዮጵያ በቡና የወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝና በጫና ውስጥም ሆና የከፍታ ጉዞዋን እንድትቀጥል እንዳስቻሏት አንስተዋል፡፡
ሀገሪቱ ለቡና ልማት ካላት እምቅ አቅም እና ምቹ ስነ ምህዳር አንፃር ገቢውን ለማሳደግ ብዙ መስራት እንደሚገባም ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የጠቀሱት።
በተያዘው በጀት ዓመት የተሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም አካላት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለዕቅዱ ስኬታማነት የተጀመረው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ዘርፉን በውጤታማነት ለመምራት ፖሊሲዎችን የማሻሻልና ሌሎች አስቻይ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም በ2014 ዓ.ም ያጋጠሙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በመቋቋም ተጠቃሽ የሆኑ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የቡናና ሻይይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ እውቅናና ተፈላጊነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ከምርት እስከ ግብይት በመቀናጀት መስራት ከተቻለ አሁን ከተገኘው የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተገንዝበናል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ዓለም የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ያሳየውን ከፍተኛ ፍላጎት መነሻ በማድረግና የቀደመውን አሰራር በመቀየር ቡናችንን በጥራት ማምረት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡