ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ቡድን ለፍጻሜ አለፈ

አዲስ አበባ ግንቦት11/2010 በምስራቅ አፍሪካ ከ18 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለፍጻሜ መብቃቱን አረጋገጠ። በተመሳሳይ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን የወከለው ከ18 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የሶማሊያ አቻውን በማሸነፍ ነገ ለሚከናወነው የፍጻሜ ጨዋታ አልፏል። ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር ስድስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ትናንት በተደረገ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የሶማሊያ አቻውን 34 ለ 20 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የበቃው። ከ18 ዓመት በታች ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታው ኬንያን 33 ለ 21 ሁለተኛ ጨዋታውን የታንዛኒያ አቻውን 42 ለ 15  በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ብሄራዊ ቡድኑ የፍጻሜ ጨዋታውን ነገ ከኬንያ አቻው ጋር ያደርጋል። በተመሳሳይ እዛው ኡጋንዳ ላይ እየተደረገ ባለው ከ20 ዓመት በታች የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአዘጋጇ ኡጋንዳ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። የሁለቱም ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ ነገ እንደሚከናወን ከወጣው መርሃ- ግብር ለማወቅ ተችሏል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ታንዛኒያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ውድድሩ እስከ ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም