ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የተለያዩ ቢሮዎችና ክፍለ ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለየዩ ቢሮዎችና ክፍለ ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁም እንስሳትና ሌሎች ድጋፎችን አደረጉ።

ድጋፉን በመከላከያ ሚኒስቴር የበጀትና ፕሮግራም ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አብዱልሰላም ኢብራሂም ተረክበዋል።

ድጋፉ የቁም እንስሳት፣ የምግብ እህሎችንና የተለያዩ አልባሳትን ያካተተ ነው።

የአስተዳደሩ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ነጂባ አክመል "እንደ ሀገር የተቃጣብንን ጦርነት በመመከት ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው "ብለዋል።

ለዚህም የአስተዳደሩ ሰራተኞችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ስራቸውን ሳያስተጓጉሉ ህዝባቸውን ከማገልገል ባለፈ ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እስኪከስሙ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ጠቁመዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የበጀትና ፕሮግራም ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አብዱልሰላም ኢብራሂም ሀገርን ለመጠበቅ እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፉን ላደረጉት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በግንባር ለተሰለፈው ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ በሁሉም አቅጣጫ ተጠናከሮ መቀጠሉን ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም