በኦሮሚያ ክልል ለተማሪዎች ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

15

መስከረም 5 / 2015 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

ቢሮው ከተለያዩ አካላት ባሰባሰበው ገንዘብ የገዛውን የትምህርት መረጃና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳት ባህል መሰረት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ዞኖችና የከተማ አስተዳዳሮች ነው ያሥረከበው፡፡  

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አብዱልሃኪም ሙሉ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ ድጋፍ ላቀረቡ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተደረገው ድጋፍ በአቅም ውስንነት ከትምህርት ገበታ የሚርቁ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡

የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ፤ ድጋፉ የትምህርት መርጃ መሳሪያ ማሟላት የማይችሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ለማገዝ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉ በቀጣይም ህብረተሰቡን እና በጎ አድራጊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማስተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ለክልሉ የተደረገው እገዛ ለበርካታ ተማሪዎች ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ቁሳቁሶችን የተረከቡ ዞኖችና የከተማ አስተዳዳሮች በቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳት ባህል መሰረት በስራቸው ለሚገኙ ወረዳዎችና ድጋፍ ለሚሹ አካላት እንደሚያሥረክቡ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቢሮው ለዚሁ ተግባር የሚውል አስር ሚሊዮን ብር አስረክቧል፡፡

ለምገባ አገልግሎት የሚውሉ ድንኳኖች፣ መጫወቻዎች፣ ደብተሮች እስክሪፕቶዎች፣ ቦርሳዎች፣ እርሳስና ሌላም ድጋፍ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም